ሀገርን ለማጽናት መስዋዕትነት የተከፈለበት ታሪካዊ ቦታ ትኩረት ተነፍጎታል።

68

ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዙሪያ ገባውን ከርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችል ኹነኛ ሥፍራ ነው። ለወታደራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ስልታዊ እና ተመራጭ እንደነበርም ይነገራል፤ መቅደላ አምባ።

አጼ ቴዎድሮስ የሥልጣን ማዕከላቸውን ከደብረ ታቦር ወደ መቅደላ ያዛወሩበት አንዱ ምክንያት ተደርጎም ይወሰዳል። ንጉሡ በዚህ ስትራቴጅክ ቦታ ላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን፣ ብዛት ያላቸው የብራና መጽሐፍትን እና ልዩ ልዩ የክብር እቃዎችን አከማችተውበት ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅት በጎንደር ይኖሩ የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ሰብስበው ያሰሩበት ወህኒ ቤትም መገኛ ነበር።

ዐፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ባካሄዱት ውጊያ ሰኞ ሚያዝያ 6/1860 ዓ.ም ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በአካባቢው ያስቀመጧቸው መጽሐፍት፣ ድርሳናት፣ የወርቅና የብር ዋንጫዎች፣ አክሊሎች፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት እና ቅርሶች ሁሉ በናፒየር በሚመራው የእንግሊዝ ጦር ተዘርፈዋል። እንግሊዞች ቅርሶቹን ከመቅደላ ለመውሰድ 15 ዝሆኖችን እና 200 በቅሎዎችን ለማጓጓዣነት ተጠቅመው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

አሁን ላይ “ሴባስቶፖል” መድፍ፣ የዐፄ ቴዎድሮስ ጊዜያዊ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽና ተቀብረውበት የነበረው መቃብር ሥፍራ ብቻ ይገኛል። የያኔው ደጃዝማች በኋላም ዐፄ ምኒሊክ ለ11 ዓመታት የመቅደላ እስረኛ የነበሩበት ቦታም ነው። ከዐፄ ቴዎድሮስ በኋላም ለወሎው ገዥ ንጉሥ ሚካኤል እንደ ወህኒ ቤት ያገለግል እንደነበር ይነገራል። ከሰገሌ ጦርነት በኋላም “አምጸዋል” ያሏቸውን ራስ አባተ ቧያለውን ለአምስት ዓመታት በእስር አቆይተውበታል። ልጅ እያሱም አምልጠው ለጥቂት ጊዜ በዚህ ቦታ መሽገው አንደነበር ይነገራል።

በአካባቢው በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደተተከለ የሚነገርለት የሰላምጌ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እና በቅዱስ ላሊበላ ዘመን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሠራ የሚነገርለት የፋል አምባ
ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንም ይገኙበታል። በ15 ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተችው የመቅደላ ማርያም እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ሚካኤል የተሠራው የተንታ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያናትም ከእድሜ ጠገቦቹ ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ አብያተክርስቲያናቱ በውስጣቸው በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የያዙ ናቸው።

የመቅደላ አምባ በርካታ ታሪካዊ ድርጊቶች የተከናወኑበት እና የተለያዩ ቅርሶችን የያዘ ቦታ ቢኾንም ታሪኩን የሚመጥን መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ አልተቻለም።

የተንታ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋኪያት አያሌው እንዳሉት የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃ እና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ችግር መኖሩ አካባቢውን ለማስተዋወቅ ፈታኝ አድርጎታል።

ለመንገድ ጥገና በየዓመቱ ከፍተኛ ወጭ እንደሚወጣ ያነሱት ኀላፊዋ አካባቢው ተራራማ በመኾኑ በክረምት ወራት በጎርፍ ጉዳት እንደሚደርስበት አንስተዋል።

ኀላፊዋ እንዳሉት ከዚህ በፊት የውጭ ጎብኝዎች ጭምር ወደ አካባቢው ይመጡ ነበር፤ ይሁን እንጅ አሁን ላይ ከወቅታዊ ኹኔታው አንጻር እና አካባቢውን የሚመጥን መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ እንቅስቃሴው ቆሟል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ይድነቃቸው ጌታነህ እንደነገሩን ደግሞ የመቅደላ አምባን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት በ2003 ዓ.ም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መድቦ የማኅበረሰብ አቀፍ ኢኮቱሪዝም ሎጅ ግንባታ አካሂዷል።

ማኅበራትንም በማደራጀት አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጅ አካባቢውን እና ታሪካዊ ዳራውን የሚመጥን መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ምክንያት የማኅበሩ አባላት ወደ ሥራ አልገቡም። የተሠሩት ሎጅዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለማልማት በ2015 ዓ.ም ከመንገድ፣ ቴሌ፣ ውኃ የመሳሰሉ አጋር አካላት ጋር ውይይት ቢደረግም እስከ አሁን ችግሩ አለመፈታቱን ነግረውናል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ እንዳሉት ደግሞ ከዚህ በፊት የአካባቢውን መሠረተ ልማት ለማሟላት የተደረገው እንቅስቃሴ የጎላ አለመኾኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ አካባቢው ተከልሎ እንዲጠበቅ፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟላለት ከአካባቢው አሥተዳደር፣ ከማኅበረሰቡ እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

መቅደላ አምባ ከደሴ ከተማ በስተ ምዕራብ 159 ኪሎ ሜትር፣ ከተንታ ከተማ ደግሞ 29 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደሴ ከተማ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።