“ቦርዱ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ግዴታ ለመፈፀም ከማንም ይሁንታ ማግኘት የለበትም፡፡” የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ

179

ባሕር ዳር: ጥር 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ያለወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉትን በመለየት ስርዓት ለማስያዝ እንደሚሠራ ምርጫ ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ከሰሞኑ አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት ፓርቲ “ምርጫ መካሄድ ያለበት መቼ ነው?” በሚል ባወጣው መግለጫ የምርጫ ጊዜው ከመወሰኑ በፊት መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ማካሄድ እንዳለበት ጠይቋል፡፡ “ድርድሩ ምርጫ ቦርድን የሚመለከት አይደለም” ያሉት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ፓርቲዎች መደራደር ያለባቸው ከመንግስት እና ከፓርላማ ጋር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ቦርዱ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ድርድሩን ተቀብሎ እና አሻሽሎ ካመጣው ምርጫ ቦርድ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ያፀደቀውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጅ 1162/2011ን መሠረት አድርጎ የምርጫ ማስፈፀሚያ ደንቦችን እና መመሪያዎችን እያወጣ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቃወሙትን አዋጅ መሠረት አድርጎ ምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ እንዲያቆም ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡

‹‹አዋጁ የፀደቀበትን ሂደት ከቦርዱ ባልተናነሰ መንገድ ፓርቲዎቹም›› ያውቁታል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ረጅም ጊዜ ተወስዶ እና በርካታ ውይይቶች ተደርገውበት በመጨረሻ በፓርላማ የፀደቀ አዋጅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አዋጅ ሆኖ ከወጣ በኋላ በሌላ አዋጅ እስኪሻሻል ድረስ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማስፈፀም እና ፓርቲዎችን ለማስተዳደር ይጠቀምበታል፡፡

“የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ግዴታ ለመፈፀም ከማንም ይሁንታ ማግኘት የለበትም” ነው ያሉት አቶ ውብሸት ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በነበራቸው ቆይታ፡፡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እና የሃገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ማስፈፀሚያ መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም ምክትል ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡ የጋራ መግባባት እና ስምምነት እንዲኖርም በዚህ ሳምንት ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋል ነው ያሉት፡፡፡

በቀጣይም የመንግስት አካላትን፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን እና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት እንደሚኖር አቶ ውብሸት አስታውቀዋል፡፡ ያለወቅቱ የሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳን በሚመለከት ቦርዱ ያለውን እይታ በተመለከተም ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ አቶ ውብሽት ሲመልሱም “በምርጫ ቦርድ ከሚሰጠው ጊዜ ውጭ የሚደረግ ቅስቀሳ መቆም አለበት” ነው ያሉት፡፡

ቦርዱ ጥናት አድርጎ እና ለይቶ ስርዓት ለማስያዝ ይሰራልም ብለዋል፡፡ “የምርጫ ህጉን ማስፈፀም በአዋጅ የተሰጠው ለምርጫ ቦርድ ነው፤ ቦርዱ ፓርቲዎችን ሊያማክር ይችላል፤ ወሳኙ ፓርቲው በመሆኑ ‘የሰጠነው ሃሳብ ሁሉ አልተካተተም’ በሚል በፓርቲዎች የሚቀርብ ቅሬታ ተገቢነት አይኖረውም” ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article“እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልጁ እንኳን ለ60 ቀናት ለ60 ሴኮንድ ‘አስደንጋጭ ቦታ ውስጥ ነው’ ሲባል ሊሰማው የሚችለው ስሜት ለታገቱት ተማሪዎችም ሊኖረው ይገባል፡፡” ኦባንግ ሜቶ
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥር 25-5-2012 ዓ/ም