“ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱ ጠቅላላ የሰብል ምርት ወደ 639 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ አስችለናል” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

40

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ ጉባዔ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት አንስተዋል። መዋቅራዊ የኾኑ እና ስር የሰደዱ ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ሀገራችን ወደፊት እንዳትጓዝ አድርገዋት ስለመቆየታቸውም ገልጸዋል።

መንግሥት ያጋጠሙ ችግሮችን ከመሠረታቸው ለመፍታት ዘርፈ ብዙ የእድገት አማራጮችን ነድፎ እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ይህም ኢኮኖሚያችን ከገባበት ቅርቃር እየወጣ በለውጥ መንገድ ውስጥ እንዲገባ እና ተከታታይ እድገቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ነው ያሉት።

በሀገራዊ ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ በነበርንበት ያለፈው ዓመት እንኳን 7 ነጥብ 5 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል ነው ያሉት። ይህ ሊኾን የቻለው የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስጋቶችን እና ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤት በማምጣቱ ነው ብለዋል።

“ኢኮኖሚያችን አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቷ ተወዳዳሪ እና ገበያ ተኮር እየኾነ ወደ ዘርፈ ብዙ እድገት እየተሸጋገረ መኾኑን አስገንዝበዋል።

እንደሀገር በግብርናው መስክ በተለይም በስንዴ ምርት ላይ የታየው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል። በዓመት ውስጥ 103 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱንም አንስተዋል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ወደውጭ የተላከበት እና ምንዛሬ የተገኘበት ዓመት ነበር ነው ያሉት። በሌሎች ሰብሎች ላይም በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል።

“ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱ ጠቅላላ የሰብል ምርት መጠን ወደ 639 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ አስችለናል” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ የመስኖ ልማት ሥራ መጠናከሩ በግብርናው ዘርፍ ለውጥ እየመጣ ለመኾኑ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በሌማት ቱሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል ብለዋል። በተለይም “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል ንቅናቄ አምራችነትን በየአካባቢው ለማስፋፋት በታየው ጥረት በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸው በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተለወጠ ሀሳብ እና በተለወጠ ልቦና ልንነሳ ይገባል” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next articleለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።