“ከእናቴ ቀጥላ እናቴ፤ ከቤተሰቦቼ የተረፈች ቤተሰቤ ናት” ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

31

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዘር ሀረጓ በዘመኑ ስደት እና ባርነት ከሀገራቸው ገፍቶ ካስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ይመዘዛል፡፡ እንዴት እና በምን ሁኔታ ለአስከፊው የባርነት ሕይዎት እንደተጋለጠች በውል ባይታወቅም በዚያ የጨለማ እና የመከራ ሕይዎት ውስጥ በተዓምር አልፋ ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀች የሕይዎት ዘመን ጽኑ፣ እስከ ሞት ታማኝ፣ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደነበረች ታሪኳ ያስረዳል፡፡

መካ የእስልምና ሃይማኖትን ስትከለክል እና የእምነቱ ተከታዮች ሲሳደዱ ሁለት ጊዜ ሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱት ሙስሊሞች መካከል ይኽች ሴት ትገኛለች፡፡ ከሀገሯ በባርነት የወጣች፤ ስለሃይማኖቷ ደግሞ ወደ ሀገሯ መልሳ መላልሳ የተሳደደች ጽኑ እና ብርቱ እናት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ እንደ ቢላልም እንደ አልነጃሽም ኢትዮጵያን እና እስልምናን በጽኑ መሰረት ካቆራኙት ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ እመቤት እሙ-አይመን ተጠቃሽ ናት፡፡

በርካቶች ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሐበሾች እና ለሐበሻ ምድር ያላቸው ፍቅር እና ክብር ከበረካ እና ከቢላል ፍቅር ጋር ይቆራኛል ብለውም ያስባሉ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ በመጨረሻው ዘመናቸው ሳይቀር “ሐበሾችን አትንኩ” እስከማለት ያደረሳቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት፤ ከስደት እስከ እንግልት ካልተለየቻቸው ኢትዮጵያዊቷ እመቤት እሙ-አይመን ካላቸው አክብሮት ሳይመነጭ አይቀርም የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡

ቤተሰቦቿ ያወጡላት እና የልጅነት መጠሪያ ስሟ በረካ አል-ሐበሽ ይባላል፡፡ እሙ አይመን ወይም የአይመን እናት ደግሞ እንደ ዓረቦቹ የሥያሜ ባሕል በመጀመሪያ ልጇ መጠሪያ ስትጠራ ነው፡፡ እሙ አይመን በረካ ወይም የአይመን እናት የአሏህን መልዕክተኛ በእምነት ተቀብላ በጽናት ያሳደገች የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለተኛ እናት ናት፡፡ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልጅነት ዘመናቸው ሞግዚት እና እንደ እናት ተንከባክባ ያሳደገቻቸው እናት ናት፡፡ ሃይማኖቷን አጥባቂ እና ነብዩን ጠባቂ በመኾኗ በብዙዎች ዘንድ አብዝታ ትወደድ ነበር፡፡

ኢትዮጵያዊቷ እመቤት እሙ አይመን በረካ ከብዙ ሴቶች በብዙው ትለያለች ያሉን የኢትዮጵያ እና ዓረቡ ዓለም ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር አደም ኢትዮጵያዊቷን እመቤት እሙ አይመንን ሲገልጿትም ይኽች ሴት ከብዙዎች መካከል ተለይታ በመከራ የጸናች፣ በቃሏ የተገኘች፣ በአሏህ ፍቅር የተገራች እና ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር እስከ ሕይዎት ዘመን ፍጻሜ ከጎናቸው ያልተለየች ብርቱ ሴት ነች፡፡

እሙ-አይመን በረካ በአሏህ መልዕክተኛ “የጀነት ሴት” ተብላ የተጠራች ብርቱ እና ታታሪ ሴት ነች፡፡ ይኽች ሴት በምድር የተቀበለችውን አደራ በሚገባ የተወጣች፤ ላመነችበት እውነት ሞትን ሳትፈራ እና ለራሷ ሳትራራ በመከራ መካከል ደጋግማ የተመላለሰች ብርቱ ሴት ነች፡፡ ይኽች ሴት የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወላጅ እናት አሚናን በመከራዋ ዘመን ከጎኗ ኾና ያበረታች፣ በእርግዝናዋ ወቅት ለአፍታ ሳትለይ የተንከባከበች፣ ስትወልድ በቅርብ የተገኘች፣ ያረሰች እና በሕይዎቷ ፍጻሜ ወቅትም በምድረ በዳ በርሃ ውስጥ መሬት ምሳ አፈር አልብሳ ለመቅበር የታደለች ኢትዮጵያዊት ሴት ናት፡፡

ፕሮፌሰር አደም እንደሚሉት በብዙ ተዓምራት መካከል የተወለዱት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይኽችን ምድር ሲቀላቀሉ በቅድሚያ ያረፉት በእሙ አይመን ክንድ ላይ ነበር፡፡ የነብዩን እናት አሚናን አልቅሳ የቀበረች፤ ልጇን ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ተቀብላ ያሳደገች እና በ63 ዓመታቸው በሞት ሲለዩ አምርራ ያዘነች የመከራ ዘመን ጽናት፤ የፈተና ዘመን ብርታት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች ይሏታል፡፡

ፕሮፌሰር አደም “አብዛኛውን ጊዜም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከበረካ አንገት አካባቢ እጃቸውን ተደግፈው ይተኙ ነበር” ይላሉ፡፡ ተመራማሪው እንደሚሉት ነብያችን ከልጅነት እስከ ዕውቀት፤ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ከሚያውቋቸው እና ከጎናቸው ካልተለዩ ሶኻባዎቻቸው መካከል እሙ አይመን በረካ አንዷ ናት፡፡ ለዚያም ይመስላል ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “ከእናቴ ቀጥላ እናቴ፤ ከቤተሰቦቼ የተረፈች ቤተሰቤ ናት” ሲሉ የመሰከሩላቸው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “የጀነት ሴት” ያሏትን እሙ አይመንን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ ከሶኻባዎች መካከል በጣም ለሚወዱት እና በስማቸው እስከመጠራት ለደረሰው ዘይድ ኢብን አልሐሪሳ ድረዋታል፡፡

ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች እሙ አይመንን እንደ አንድ የእስልምና ሃይማኖት ባለውለታ ስናያት ኢትዮጵያዊ በመኾኗ ብቻ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰር አደም እስልምና በፈተና፣ በመሳደድ እና በችግር ላይ በነበረበት ወቅት ለቃሏ እና ለሃይማኖቷ ጹኑ ኾና በመገኘቷ ነበር ይላሉ፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ለሃይማኖት መጽናትን፣ ለሀገር መበርታትን፣ ለቃል መገኘትን እና ላመኑበት መሞትን ከእሙ አይመን ሊማሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመውሊድ በዓል እየተከበረ ነው።
Next articleለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል በሠላም አደረሳችሁ!