“መውሊድ ለዓለም ሰላም የተበሰረበት በመኾኑ ስለሰላም ጸሎት ይደረግበታል” የታሪክ ተመራማሪ ሼህ ኑርሁሴን ሙስጠፋ

9

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)መውሊድ ማለት የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱበት ቀን ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ሀገራት የተለያየ ስያሜ ተሰጥቶት እናገኘዋለን ፤ ለአብነት ቱርካውያን መውሊድ ሸሪፍ ሲሉት ፈሪሳውያንም ሚላድ ፓምባረ ኢክራም ሲሉ ይጠሩታል፡፡

በተለያዩ ሀገራት የተለያየ ስያሜ ይኑረው እንጂ የሁሉም ትርጓሜ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት ማለት ነው፡፡ ጎርዶን ዲ. ኒውባይ በ2006 እ.ኤ.አ ባሳተሙት ኮንሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ ፊ-ኢስላም (ገጽ 146 እና 147) “የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት ቀን የውዳሴ ግጥሞችን በማቅረብ ፣ በእለቱ ቁርዓን በመቅራት፣ ስጦታ በመለዋወጥ ያስታውሱታል፡፡” በብዙ ቦታዎች ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ይከበራል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከተወለዱ ከ40 ዓመታት በኋላ የተወለዱበትን ቀን በጾም ያከብሩ ነበር፤ ለምን በጾም እንደሚያከብሩት ሲጠየቁ “ይህች ቀን የተወለድሁባት ቀን ናት” በማለት ያከብሩ እንደነበረ የታሪክ ተመራማሪው ሼህ ኑርሁሴን ሙስጠፋ ነግረውናል፡፡

ሰዎች ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) መውደዳቸውን ለመግለጽና ሰዎችን ለመርዳት በመፈለጋቸው በጾም ያከብሩት የነበረውን በዓል ምግብና መጠጥ የሚቀርብበት እና እየተበላ እየተጠጣ በኅብረት እንዲከበር አድርገውታል። ይህም በጾም ወቅት ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ነገሮች አቅበው ስለሚኖሩና ሰዎችን ማገዝ ስለማይቻል ሰዎች ተሰባስበው በጋራ በደስታ በዓሉ መከበር መጀመሩን ሼህ ኑርሁሴን ነግረውናል፡፡

ማንኛውም ሰው ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እንደነፍሱ እንዲወድም ቁርዓን ያዛል ፤ ስለኾነም ማንኛውም ሰው ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) መውደዱን ለመግለጽ በተወለዱበት ቀን በዓላቸውን ለማክበር ወደ መስጂዶች በመሄድ ሃይማኖታዊ ተግባራትን ይፈጽማልም ብለዋል ሼህ ኑርሁሴን፡፡

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “መውሊድ ለዓለም ሰላም የተበሰረበት በመኾኑ የተራበ ይጠግብበታል፣ የተጠማ ይጠጣበታል፣ ፈጣሪን ለማስታወስም ጸሎት ይደረግበታል” ሲሉ ገልጸዋል ሼህ ኑርሁሴን፡፡

እስልምና ሃይማኖት ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከት እምነት በመኾኑ የሃይማኖቱ ተከታዮች ለሌሎች እዝነት በማድረግ፣ በማብላትና በማጠጣት ሊያከብሩት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ነብዩ የሰላም አባት”
Next articleየመውሊድ በዓል እየተከበረ ነው።