
ባሕር ዳር፡- ጥር 16/2012ዓ.ም (አብመድ) የግንባታ ቁሳቁስ መዘግየት በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሥጋት ሆኗል።
የጣና በለስ የተቀናጀ የሥኳር ልማት ፕሮጀክት ግንባታው 2003 ዓ.ም ላይ ነበር የተጀመረው፡፡ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተጀመረው ፕሮጀክቱ የግንባታ ጥራት ችግር ከመስተዋሉ ባለፈ መዘግየቱ በመረጋገጡ የተነሳ በ 2010 ዓ.ም እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ይጠናቀቃሉ ከተባሉበት ጊዜ በእጅጉ ከዘገዩት የሀገሪቱ የሥኳር ፕሮጀክቶች አንዱ ነው የጣና በለስ የተቀናጀ የሥኳር ልማት ፕሮጀክት። ከዚህ ውስጥ ጣና በለስ ቁጥር አንድ የሥኳር ፋብሪካ ግንባታን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በሚል “ካምስ” ለተባለ የቻይና ኩባንያ ውል ተሰጥቷል።
በኩባንያው የኘሮጀክቱ ዋና ተጠሪ ዛንግ ሚንግ ያንግ የፋብሪካውን ግንባታ ለማካሄድ በአውሮፖውያኑ 2019 መስከረም ወር ውል እንደተወሰደ ተናግረዋል። በውሉ መሠረት ምእራፍ አንድን በስምንት ወራት፣ ምእራፍ ሁለትን ደግሞ በስድስት ወራት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል። ይህም ማለት የምእራፍ አንድ የጣና በለስ ቁጥር አንድ የሥኳር ፋብሪካ ግንባታ በያዝነው ዓመት ግንቦት ላይ መጠናቀቅ ይጠበቅበታል።
የግንባታ ቁሳቁስ በጉዞ ላይ እየዘገዩ በሥራው መዘግየት መፈጠሩን የተናገሩት የፕሮጀክቱ ዋና ተጠሪው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል። እስካሁን 85 ከመቶ የሚደርሰው ሥራ መጠናቀቁንም ነው የገለፁት።
የኢፌዴሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪያል ምህንድስና መምህር ዳንኤል ቅጣው (ፕሮፌሰር) ደግሞ የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሕዝቡ ከሥራው ተጠቃሚ እንሆናለን ብሎ እስከአሁን ምንም ያገኘው ጥቅም አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ፋብሪካው ግንቦት ላይ የማምረት ሙከራ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ሲሉም አሳውቀዋል። ፋብሪካው ሥራ መጀመር ከነበረበት ጊዜ በመዘግየቱ የተነሳ የሸንኮራ አገዳው በየጊዜው እየተመነጠረ ነው። በዚህም በየጊዜው በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት እየባከነ መሆኑን አብመድ ሲዘግብ ቆይቷል።
የጣና በለስ የተቀናጀ የሥኳር ልማት ፕሮጀክት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ነው እየተገነባ ያለው፡፡ፕሮጀክቱ በ40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ ሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት እንደሚጠቀም ይጠበቃል፡፡ በመጪው ግንቦት ወደ ሙከራ ምርት ይገባል የተባለውን ጨምሮ ፋብሪካዎቹ ወደ ሙሉ ምርት ሲገቡ እያንዳንዳቸው በዓመት 2 ሚሊየን 420 ሺህ ኩንታል ሥኳር እና 20 ሚሊየን 827 ሺህ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የፋብሪካው የግንባታ ሂደት በፌዴራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች እየተጎበኘ ነው።
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ