10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይደረጋሉ፡፡

215

ባሕር ዳር፡- ጥር 15/2012ዓ.ም (አብመድ) የ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ይደረጋሉ፡፡

ነገ ጥር 16/ 2012 ዓ.ም ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ ስሑል ሽረ ከጅማ አባ ጅፋር፣ ሰበታ ከተማ ደግሞ ከሐዋሳ ከተማ ይገናኛሉ፡፡ ጨዋታዎቹ በተመሳሳይ 9፡00 ይደረጋሉ፡፡ እሁድ ጥር 17/2012 ዓ.ም በርከት ያሉ ጨዋታዎች ሲደረጉ አጼዎቹ በሜዳቸው ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ፡፡ በ15 ነጥብና በ9 ንጹህ የግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አጼዎቹ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ነው ከሲዳማ ቡና ጋር የሚጫወቱት፡፡

ሲዳማ ቡና በ9ኛ ሳምንት በቡና ደርቢ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአዲስ አበባ ስታዲዬም ተጫውቶ 2ለ1 መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ፋሲል ከነማም ወደ ትግራይ ተጉዞ በስሑል ሽረ 2ለ0 መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ከሽንፈት የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች እሑድ ጥር 17 ጎንደር ላይ በአጼ ፋሲለደስ ስታዲዬም ይናኛሉ፡፡ አጼዎቹ በዚህ የውድደር ዓመት በሜዳቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፈዋል፡፡ ከሌሎች የፕሪሚዬር ሊጉ ቡድኖች በተለዬ በርካታ ንጹህ ግብ ያለው ቡድንም ነው፡፡

ጨዋታው ቀን 9፡00 ይደረጋል፡፡ ሌሎች ጨዋታዎች እሁድ ጥር 17/ 2012 ዓ.ም ሲደረጉ ወላይታ ዲቻ ከመቀሌ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባሕር ዳር ከነማ እና ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታዎቹ በተመሳሳይ ቀን 9፡00 ይደረጋሉ፡፡

ፕሪሚዬር ሊጉን የአምናው አሸናፊ መቀሌ 70 እንደርታ በ19 ነጥብና በ5 ንጹህ ግብ ሲመራው ፋሲል ከነማ በ15 ነጥብና በ9 ንጹህ ግብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ስሑል ሽረ በ15 ነጥብ ያለምንም ንጹህ ግብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባሕር ዳር ከነማ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ አዳማ ከተማ ፣ሀድያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ ቡድኖች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፋሲል ከነማ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የምስጋና የምሰክር ወረቀት ልኳል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ፋሲል ከነማ እና ባሕርዳር ከነማ በየሜዳቸው የሚያደርጓቸውን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በሁሉም ሚዲዬሞች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ፋሲል ከነማም እግር ኳስ ቡድንም አብመድ በመላው ዓለም ለሚገኙ ደጋፊዎቹ በቀጥታ ስርጭት በማድረሱ እና ለስፖርቱ ዕድገት እያደረገ ላለው አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርቧል፡፡ በቀጣይም ይህ አይነት ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቀው እግር ኳስ ቡድኑ ወደፊትም በጋራ መስራት እንደሚፈልግ በላከው የምስጋና ወረቀት አስታውቋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

Previous articleእስራኤል የቤተ እስራኤላውያኑን መካነ መቃብር የቱሪስት መዳረሻ ልታደርግ ነው፡፡
Next articleአርሶ አደሮች እና ከተሜው ስለ ምርጫው ተስፋም ሥጋታቸውን ተናገሩ፡፡