“እናገለግልሽ ዘንድ ስለተፈጠርን እናመሰግናለን!”

27

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አኹናዊውን ቅንጡ ተፈጥሮዋን አዝጋሚ በኾነ የዘመናት ሂደት የተላበሰችው በእያንዳንዱ ግለሰብ ኅሊና ውሰጥ ነው ብለው የሚያስቡ የሰብዓዊ ስሜት (ሰብጀክቲብ አይዲያሊስት) ሐሳባዊያን አሉ።

እነዚህ ሐሳባዊያን ባሉበት በዚህ ዘመን ከእያንዳንዱ ግለሰብ ኅሊና ዕውን የሚኾነው የአገልጋይነት ስሜት እና መንፈስ ዓለምን ራሷን የመቀየር አቅሙ እና ተፅዕኖው የጎላ ነበር ተብሎ ይታመናል። ምድራችን በአገልጋዮቿ እየተገለገለች ከትናንት እስከ ዛሬ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት፡፡

ከቀደምቱ የድንጋይ ዘመን እስከ አኹናዊው የመረጃ ዘመን በዘለቀው የምድራችን እድሜ ዓለም ለሰብዓዊ ፍጡር ከመኖሪያ እስከ መቀበሪያ ባለውለታ ኾና ዘልቃለች። ከእጽዋት እሰከ እንስሳት በምድር ላይ ያሉ ፍጡራንም ለምድር ህልውና ብድር መላሾች ናቸው።

ተፈጥሮ እና ፍጡር አንዱ ሌላውን እያገለገሉ፤ አንዱ በሌላውም እየተገለገለ እስከዚህ ዘመን ደርሰዋል። አገልጋይነትም ከተፈጥሮ እና ፍጡር የመጀመሪያ መሥተጋብር ጀምሮ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ቅቡልነት ያለው ሰናይ ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ዓለም ላይ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ጥሩ የኾነው ነገር ምንድን ነው ከተባለ በቅንነት ማገልገል ነው፡፡

አሁን አሁን ቁሳዊ አስተሳሰብ ሚዛን በደፋበት በዚህ ዘመን ሳይቀር “እናገለግልዎ ዘንድ ስለፈቀዱልን እናመሰግናለን” የሚሉ ወርቃማ እና ሳቢ ንግግሮችን በየቦታው ማዳመጥ እንግዳ ነገር አይደለም። ቅን አገልጋይነት የመንፈስ ልዕልናን ከማላበሱም በላይ “መታዘዝ ከመስዋዕትነት ይበልጣል” የሚል መንፈሳዊ ቅቡልነት የተሰጠው ቅዱስ ኅላፊነትም ተደርጎ ይወሰዳል። ማገልገል ክብር ነው የሚባለውም አገልጋይነት ትህትናን ጫማዋ፤ ተጠያቂነትን መልህቋ ያደረገች ሐዋሪያዊም ዓለማዊም ተልዕኮ በመኾኗ ነው፡፡

በየትኛውም ሚዛን ቢለካ ደግሞ ኢትዮጵያን ማገልገል የተለየ እና እጥፍ ድርብ ትርጉም አለው። ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል አዝማናት ሁሉ ያገለገሏትን የማትረሳ ሀገረ መዝገብ እና ሀገረ ማሕደር ናት፡፡
ከነገሥታት እስከ መንግሥታት፣ ከወታደር እስከ አርሶ አደር፣ ከመምህር እስከ ደቀመዝሙር፣ ከአዛውንት እስከ እመበለት እና ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትናንት በኢትዮጵያ ላይ ያረፉ በጎ አሻራዎች ሁሉ ፈጽሞ አልተዘነጉም፡፡ ትናንት በቅንነት ያገለገሉ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በባለውለታነት በየአውዱ ሁሉ ይታወሳሉ፡፡

ኢትዮጵያን እንደ ሸክላ አቡክተው፣ እንደ ብረት አቅልጠው፣ እንደ ወርቅ አንጥረው፣ እንደ ብራና ፍቀው፣ እንደ ሰይፍ ስለው፣ እንደ ጋሻ አጠንክረው፣ እንደ ላሊበላ ጠርበው እና እንደ ፋሲል አንጸው ያስረከቡንን ቀደምቶቻችን የልብ አገልጋዮች ነበሩ። ኢትዮጵያን በቅንነት ማገልገል ከምድራዊ ሃሴቱ በላይ መንፈሳዊ በረከቱ ብዙ እና የተትረፈረፈ ነው።

እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት ከ1711 እስከ 1776 የኖረው እንግሊዛዊው የሥነ-መንግሥት እውቅ ፈላስፋ ዩሂም ዴቪድ “የዕውቀት ፋይዳ የሚለካው ለተግባር በሚሰጠው አገልግሎት እንጂ በረቂቅነቱ ወይም በውስጣዊ ጥልቀቱ አይደለም” ይላል።

ሀገር በጥበብ እና በአገልጋይነት እንጂ በምኞት እና በህልም አታድግም፡፡ እንኳን ሀገር ሰው ራሱ እንኳን ለማሳደግ በመጀመሪያ በውስጡ ቅን የሆነ የአገልጋይነት ስሜት ማዳበር ይኖርበታል፡፡ ከህልም ዓለም የወጣ፣ በተግባር የተገለጠ እና በቅንነት የሚመራ አገልጋይነት የእያንዳንዱ ግለሰብ የሕይዎት መርህ ሲኾን ውጤቱ አመርቂ ይኾናል፡፡

በኢትዮጵያ የልዩነት ጌጥ እና የዘመን ሥሌት ፈርጥ ወርሃ ጳጉሜን መግቢያ ላይ ሆኾነን ስለ አገልጋይነት ቀን ስናስብ “እናገለግልሽ ዘንድ ስለተፈጠርን እናመሰግናለን!” እንል ዘንድ ምክንያቶቻችን ብዙዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ወታደር በሕይዎቱ፣ ምሁር በዕውቀቱ፣ አርሶ አደር በምርቱ እና የሃይማኖት አባት በጸሎቱ ሁሉም በየድርሻው የሚያገለግላት ሀገር ናት፡፡ ሀገርን ማገልገል ልክ እንደ ጅረት ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ የሚጸና መሠረታዊ ተግባር ነው፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ለሚተጉ ምስጉን አገልጋዮች ምሥጋና እንደሚገባቸው የባሕር ዳር ተገልጋዮች ተናገሩ።
Next articleየጤና ሚኒስቴርና ተጠሪተ ቋማቱ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ነጻ የጤና ምርመራ እየሰጡ ነው።