
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በ12 ወረዳዎች የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ መኾኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡
የመምሪያው ተወካይ ኀላፊ ይርጋ ጌትነት እንዳሉት ከነሐሴ 23 እሰከ ጷጉሜን 3/2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ መርሐ ግብር ቢወጣም በዞኑ በነበረው የሕግ ማስከበር ምክንያት መዘግየቱን ነው የገለጹት፡፡
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ ምዝገባ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በዞኑ በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከታቀደው ከ647 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች ውስጥ በአራት ቀናት ውስጥ ከ109 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡
ችግር የነበረባቸው እስቴ እና ፎገራ ወረዳም ወደ ሰላም በመመለሳቸው ከጷጉሜን 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ እንደሚጀምሩም ገልጸዋል፡፡
አቶ ይርጋ እንዳሉት የመማር ማስተማር ሥራውን በታቀደው ጊዜ አስጀምሮ በታቀደው ጊዜ ለማጠናቀቅ ተማሪዎች በወቅቱ ተመዝግበው በትምህርት ሳምንት ላይ ሊሳተፉ ይገባል፡፡
ዞኑ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ግንባታ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ እና አጋር አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ባለፉት ዓመታት በክረምት ወራት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ግንባታ ሥራ በማከናወን ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እና የምዝገባ ሥርዓቱን በወቅቱ በማከናወን ውጤታማ ሥራዎች የተሠሩበት ወቅት እንደነበር ያነሱት ተወካይ ኀላፊው በተያዘው የክረምት ወራት በዞኑ በነበረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ችግር ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!