ለ70 ሺህ 400 ሥራ አጥ ወጣቶች የገጠር መሬት እንደሚያቀርብ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።

121

ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት ለ70 ሺህ 400 ሥራ አጥ ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት መሬት በማቅረብ በገጠር ያለውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጿል።

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሥራ አጥ ወጣቶች በልዩ ልዩ የግብርና ዘርፎች እንዲሰማሩ ለማድረግ የተዘጋጀውን መሬት የማስተላለፍ ሥራ እንደሚያከናውን የቢሮው ገጠር መሬት አሥተዳደርና ካዳስተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታከለ ሃብቴ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የመኸር ሰብል እንደተሰበሰበ ለወጣቶች የሚተላለፈውን መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ ወደ መሬት ባንክ ገቢ የማድረግ ሥራ ይጀመራል። አሠራሩን እና የመሬት አቅርቦቱን በተመለከተ በተዋረድ ከሚገኙ የመሬት ባለሙያዎች እንዲሁም ከወረዳ እና ከዞን አመራሮች ጋር ውይይት ስለመደረጉም አቶ ታከለ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በገጠር ውስጥ ያለአግባብ የተያዙ መሬቶችን የመለየት ሥራ ይከናዎናል ነው የተባለው።

ከመሬት አጠቃቀም ሥርዓቱ ውጭ በኾነ መንገድ በግለሰቦች የተያዙ መሬቶች፤ ለአብነትም ከጥሎ ሂያጅ የተገኘ፣ ከወራሽ አልባ የተገኘ እና ከመንግሥት ባለቤትነት ነፃ ኾነው የሚገኙ መሬቶች ለወጣቶች የሚተላለፉ ይኾናል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ በታቀደው መሰረትም 24 ሺህ 125 ሄክታር መሬት በቋሚና ጊዜያዊነት ለወጣቶች እንደሚተላለፍ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በቋሚነት የሚረከቡ ወጣቶች ተገቢውን የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ የሚሰጣቸው ሲኾን በጊዜያዊነት የሚወስዱት ደግሞ ከሚወሰነው የጊዜ ገደብ በኋላ ለሌሎች ወጣቶች ያስተላልፋሉ። በቋሚነት ተረክበው ተገቢውን የይዞታ ማረጋገጫ የሚያገኙ ወጣቶች በወሰዱት መሬት ዋስትናነት ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከወል መሬት ውጭ የኾኑ እና በመንግሥት ይዞታ ውስጥ ያለልማት የተቀመጡ መሬቶችም ለዚሁ ተግባር እንደሚውሉ አቶ ታከለ ተናግረዋል። የገጠር መሬትን ተጠቅሞ ሥራ አጥነትን የመቀነስ ተግባር እውን እንዲኾን መሬት ቢሮ ከክልሉ ሥራና ስልጠና ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማበረታታት ገንቢ ሚና ይጫወታል” አቶ ካሳሁን ጎፌ
Next article“ለሀገር የቆመ፣ ለሠንደቅ የቀደመ-ሕዝብ”