“ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማበረታታት ገንቢ ሚና ይጫወታል” አቶ ካሳሁን ጎፌ

52

ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማበረታታት ገንቢ ሚና እንደሚጫወት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከወጪ ንግድ ላኪ ማኅበራት እና ላኪዎች ጋር የወጪ ንግድ ልማት ስትራቴጂን አስመልክቶ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገራትን መቀላቀሏ የወጪ ንግዱን ለማበረታታት አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በተጨማሪም ከሀገራት ጋር ያላትን የውጪ ንግድ ግንኙነት በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ ይበልጥ እንዲያድግ ያግዛታል ነው ያሉት።

በዚህም የብሪክስ አባል ከሆኑ ሀገራት ጋር በቅርበት በመስራት የወጪ ንግዱን ለማበረታታት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በመጪዎቹ ወራቶች የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቁመው፥ በስትራቴጂ የሚመራ የወጪ ንግድ ሥርዓት መፍጠርም ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽ የሆነ ብሔራዊ የወጪ ንግድ ስትራቴጂ ሳይኖር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዎንታዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር መሆኗን በመጠቆም፤ ለዚህም የወጪ ንግድ ማነቆዎችን በጥናትና ምርምር የታገዘ መፍትሔ አመላካች ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ሥራ መግባት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው ሲዘጋጅም በመንግሥት ውሳኔ መሰረት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ እና ምርታማነት ለማበረታታት ታሳቢ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ መነሻነትም የወጪ ንግድ ሥርዓቱን ማበረታታት የሚያስችል ግልጽ የወጪ ንግድ ስትራቴጂ መቀረጹንና ለውሳኔ መቅረቡን አስታውቀዋል።

የምክክር መድረኩም በስትራቴጂው ላይ መግባባት በመፍጠር ውጤታማ የወጪ ንግድ ልማትን ለማሳለጥ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩም የወጪ ንግድ ልማት ስትራቴጂ እና ከዚህ ቀደም የነበሩ አፈፃፀሞች፣ አስቻይ ሁኔታዎችን የሚዳስሱ ጸሑፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

ብሪክስ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ባካሄደው 15ኛው ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ጥምረቱን እንድትቀላቀል መወሰኑ ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሽማግሌ እና ሽምግልና ፈጽሞ ባልጠፋባት ኢትዮጵያ የግጭት ነጋሪት ለምን አብዝቶ ይጎሰማል”
Next articleለ70 ሺህ 400 ሥራ አጥ ወጣቶች የገጠር መሬት እንደሚያቀርብ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።