
አዲስ አበባ: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በበዓላት ወቅት የሚስተዋለውን የፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የተሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
እንደ ሀገር ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ባለፉት ሦስት ወራት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ በተደረጉ ጥብቅ የቁጥጥር ሥራዎች 395 ሺህ በሚኾኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ ገልጸዋል።
በንግድ ሰንሰለቱ የተሰማሩ ሕገ ወጥ ደላሎች ፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ፣ሀገራዊው የፀጥታ ችግርና ዓለማቀፋዊው ሁኔታ በሸቀጦች እና ምርቶች ላይ ለታየው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት መኾናቸውንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱት።
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኢንዶክትሪኔሽን ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ቀፀላ ሸዋረጋ ከቀናት በኃላ ለሚከበረው የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ከ11ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ፣ዱቄትና ሽንኩርት በአማራ ፣በድሬድዋ ፣በጋምቤላ ፣በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያና በሱማሌ ክልሎች በንግድ ሥራዎች በኩል መሰራጨት ጀምረዋል ብለዋል።
መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ መሰረታዊ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቹ ማኅበረሰብ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀደም ብሎ መሰራጨት እንደሚጀምሩም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!