
አዲስ አበባ: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምረቱ ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ የተሰኘ የፋይናንስ ተቋም ያለው ሲሆን ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የልማት ብድሮችን ማቅረብ የሚችል ነው ተብሏል።
ከተቋቋመ 14 ዓመታት የኾነው የአምስት አባል ሀገራት ጥምረት ብሪክስ ከጊዜ ወደጊዜ ተደማጭነቱን እያሳደገ በዚህ ዓመት ጉባኤው 6 ሀገራትን በአባልነት አካትቶ አቅሙን እያሰደገ መጥቷል።
ብሪክስ በዓለም ፖለቲካ አሰላለፍ የደቡባዊ ዓለም ክፍል እና ሰሜን ሲሉ የሚከፍሉትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ አሰላለፍ የማስተካከል አሰላለፍን ይዞ መጥቷል።
በዋናነት ይህን አሰላለፉ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነትን ሚዛን ማስጠበቅ መኾኑን በጉዳዩ ላይ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ ዲፕሎማት እና የፖለቲካ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰሩ ብሩክ ኀይሌ በሻህ አብራርተዋል።
ብሪክስ ሲመሰረት 3 ዓለማዎች ያሉት ነው። እውነተኛ አለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ፣ ፍትሐዊ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገትን ማምጣት እንዲሁም አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍን መፍጠር የሚሉ ናቸው ብለዋል::
እንደፕሮፌሰር ብሩክ ገለጻ ነባሮቹ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግዙፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች የሚታዘዙ በመኾኑ ለታዳጊ ሀገራት ፍትሐዊ የገንዘብ አቅርቦት የላቸውም። ብሪክስ ይህን ፍትሐዊ አሠራር ላምጣ ሲል “ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ” የተሰኘ ባንክን አቋቁሞ ነው።
ይህ ባንክ እስከአሁንም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድርን ሰጥቷል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን ዶላርን ከጥቅም ውጭ ማድረግ አለብን ሲሉ በተደመጡበት 15ኛው ጉባኤ ጥምረቱ አዲስ ገንዘብ የሚያስተዋውቅ ከኾነ የሚተገበረው በዚህ ባንክ በኩል ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ባንክ በኩል የተሻለ እገዛ የማግኘት እድል እንዳላት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን ዝግጁ በማድረግ በኤንዲቢ በኩል የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ እንዲሁም ሌሎች ቁልፍ የልማት ተግባራት ብድር የማግኘት እድል አላት ብለዋል።
ነባሮቹ የባለብዙ አምድ የዲፕሎማሲ ጥምረቶች አዳዲሶቹን የዓለም ኢኮኖሚ ክስተት ሀገራት አላካተቱም ብቻ ሳይኾን እንዲያካትቱ የሚያስችላቸውን ክፍት አሠራር አልተውም።
እናም ብሪክስ አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ጫና ፈጣሪ ጉልበትን ይዞ መጥቷል። ይህንን አሠራር ለማካተት ጥናት ከጀመረ 25 ዓመታት የኾነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከአሁን ብድርን አልሰጠም።
ይሁንና የ78 ዓመት እድሜ ጠገብ ተቋም ራሱን እንዲያጤን ግን ጊዜው የመጣበት ይመስላል ብለዋል ፕሮፌሰር ብሩክ። ስለዚህም በፀጥታው ምክርቤት ውስጥ በርካታ ሀገራት መካተት የሚያስችለውን አሠራር መዘርጋት የሚያስገድደው ጊዜ መኾኑን አንስተዋል።
በዚህ ሁሉ ዙሪያ ገባ ግን ፈርጣማ ተደማጭነትን የሚፈጥሩበት እድልን ብሪክስ ለአባል ሀገራቱ ይዞ መጥቷል።
እንደአውሮፓ ኅብረት ሁሉ ወደዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ከመግባታቸው በፊት የብሪክስ አባል ሀገራት የሚጠቅማቸውን አቅም ይዘው በመግባት ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲችሉ ጠንካራ ጥላ መኾን የሚያስችል ጥምረት መኾኑን አንስተዋል
ከወዲያ 85 በመቶ የካፒታል በጀት ብድሯን ከቻይና የምታገኘው ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ከሩሲያ ጋር ላሰረችው የምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ከወዲህ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ከፍተኛ የንግድ እና የባህል ትስስር ላለት የባለብዙ አምድ ባለታሪኳ፣ ብሪክስ ለዚህ ሁሉ ትስስር በመፍጠር መልካም አጋጣሚን ለኢትዮጵያ ይዞላት መጥቷል ተብሏል።
በአንዱአለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!