
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ምዕራባዊያን የዘመን ቀመር 2009 ላይ በአራት ሀገራት የተቋቋመው ብሪክስ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና መሥራች ሀገራቱ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በተቋቋመ በዓመቱ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን አካትቶ ተደራሽነቱን እስከ አፍሪካ ልሳነ ምድር ድረስ ዘረጋ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ለዘመናት የፀናውን ምዕራባዊያን ሠራሹን ምጣኔ ሃብታዊ ይዞታ ለመገዳደር እንዳለመ የሚነገርለት ብሪክስ አሁናዊ ቁመናው የታለመለትን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ብቃት ላይ ደርሷል የሚሉት ብርካቶች ናቸው፡፡
እስካሁን በአጠቃላይ 40 በመቶ የዓለም ሕዝብ ቁጥርን የሚሸፍኑ ሀገራትን ለማካለል የሚያስችለውን ውሳኔ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ስብሰባው ያሳለፈው ብሪክስ አሁን ላይ 32 በመቶ ዓመታዊ የምርት እድገትን ይሸፍናል እየተባለ ነው፡፡ ከጥር 2024 አዲስ ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች እና አርጀንቲናን በአባልነት የሚያካትተው ብሪክስ የቡድን-7 አባል ሀገራትን የመገዳደሩ ጉዳይ አይቀሬ እየኾነ መጥቷል ተብሏል፡፡
በዘንድሮው የደበብ አፍሪካ ስብሰባው የአባል ሀገራቱን ቁጥር በእጥፍ የጨመረው ብሪክስ ምዕራባዊ ዘመሙን የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ ስሪት የመዘወር እድሉ እምርታዊ የኾነ ይመስላል ተብሏል፡፡
ዕውቁ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን ዘመናትን ያስቆጠረው ምጣኔ ሃብታዊ ስሪት እስከወዲያኛው እየተቀለበሰ ይመስላል ይላሉ፡፡ ምሥረታው እና ሂደታዊ እድገቱ ዓለም ትናንት የነበረውን መዋቅራዊ ስሪት ረስታ ለአዲስ አሰላለፍ እንድትዘጋጅ የማንቂያ ደወል ነው የሚሉት ፍሪማን የሰሞኑ ስብሰባ ውሳኔ ብሪክስ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡
የብሪክስ 15 ዓመታት ጉዞ አዲስ የሥልጣኔ ጮራ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ከመጭው የምዕራባዊያኑ አዲስ ዓመት ጀምሮ የእድገቱን ሌላ ምዕራፍ ይጀምራል ይላሉ፡፡ “ብሪክስ የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ ሥሪት ማርሽ ቀያሪ ክስተት ኾኗል” የሚሉት ሎውረንስ ፍሪማን ለዓለም በተለይም ደግሞ ለአፍሪካ አህጉር አዲስ እድል እና ተስፋ ይዞ እንደመጣ አንስተዋል፡፡
በቅድመ ኹኔታ ላይ የተመሰረተውን ምዕራብ ዘመም ምጣኔ ሃብታዊ የበላይነት እየተገዳደረ ነው የተባለለት ብሪክስ ከደቡብ ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ ላሉት የምሥራቁ ዓለም ሀገራት አማራጭ የእድገት አጋዥ እንደሚኾን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካ የበላይነት ለማስቀጠል ሲያሻቸው እጃቸውን የሚያስረዝሙትን፤ ሲፈልጉ ደግሞ የሚሰበስቡትን የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ተቋም ( አይ ኤም ኤፍ)ን ሚና ብሪክስ የመገደብ አቅም እየፈጠረ ነው የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ፍሪማን በቅርቡ ሌላ ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሃብት ስብስብ የመመልከታችን ጉዳይ አይቀሬ እየኾነ መጥቷል ብለዋል፡፡
የብሪክስ እድገት ከጽንሰ ሃሳብ አልፎ ገቢራዊ ለውጦችን አሳይቷል የሚሉት ፍሪማን ከተቋቋመበት 2009 እ.አ.አ አምስት ዓመታት በኋላ የራሱን የልማት ባንክ እስከ መመሥረት እንደደረሰ አንስተዋል፡፡
የምዕራባዊያን የበላይነትን ናፋቂዎች በብሪክስ ላይ ብዙ ትቺቶችን ቢሰነዝሩም ከምንም የተነሳ ታላቅ ማንነት እየገነባ መኾኑን ግን ምዕራባዊያኑ ሳይቀር ገብቷቸዋል ነው ያሉት፡፡ ትብብር፣ አብሮ ማደግ እና አማራጭ መፍትሔዎችን ማመላከት የብሪክስ መቋቋሚያ መርሆዎች መኾናቸው ደግሞ ዓይኖች ሁሉ ብሪክስ ላይ እንዲመለከቱ አስገድዷል ይላሉ፡፡
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ፍሪማን እንደሚሉት ላለፉት 14 ዓመታት በአፍሪካ አህጉር የብሪክስ አባልነትን ደቡብ አፍሪካ ብቻዋን ይዛ ብትቆይም በጆሀንስበርጉ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን እና ግብጽን አባል ሀገራት ማድረጉ ለአህጉሪቷ አዲስ ተስፋ እና አማራጭ እንድትመለከት ረድቷታል ብለዋል፡፡ ሁለቱም ሀገራት በአህጉሪቷ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ተስፋ ሰጭ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ያላቸው ሀገራት ናቸው የሚሉት ተንታኙ በተለይም ኢትዮጵያ በሌላ የኢኮኖሚ አማረጭ እንድትመለከት እድል ሰጥቷታል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!