
አዲስ አበባ: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበርና በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማራው ሳፋሪኮም በጋራ ለመሥራት የሥራ የስምምነት ውል ተፈራርመዋል።
ዓባይ ባንክ ከሳፋሪ ኮም የ ኤም.ፒ ኤሳ ጋር የሥራ ስምምነት ውሉን መፈራረሙ ዓባይ ባንክ የሳፋሪኮም ኤም.ፒ ኤሳ ሱፐር ኤጀንት በመኾን የሞባይል ባንኪንግ እና የኤጀንት ባንኪንግ ሥራዎችን በተቀላጠፍ ኹኔታ ማሳለጥ ያስችለዋል ተብሏል።
በተግባር ሂደት ከሚፈጠሩ አስቻይ ኹነቶችም:-
👉 ደንበኞች ከዓባይ ባንክ ሂሳባቸው ወደ ኤም.ፒ ኤሳ ሂሳባቸው ማስተላለፍ እንዲችሉ ያደርጋል ፡፡
👉 ከኤም.ፒ ኤሳ ሂሳባቸው ወደ ዓባይ ባንክ ሂሳባቸው ገንዘብ ማስተላለፍ ያስችላል፡፡
👉 የአገልግሎት ክፍያዎችን እንዲከፍሉ ያስችላል፡፡
👉 የሂሳብ መረጃዎችን ማየት ያስችላል ፡፡
👉 የአየር ሰዓት እንዲገዙ እና ሌሎችንም የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርአቱ ላይ የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠና የሳፋሪኮም ኤም.ፒ ኤሳ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፖል ካቫቩ የተጀመረዉን የሥራ አጋርነት ስምምነት በማጠናከር ደንበኞችን የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት እና የክፍያ ሥርአት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በማስቻል የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!