
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015/2016 የመኸር እርሻ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ቢሮው ገልጿል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አጀበ ስንሻው አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን አንስተዋል። ከታቀደው ውስጥ 92 በመቶው በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ክልሉ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት የመረጃ ቅብብሎሽ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉንም ምክትል ቢሮ ኀላፊው አንስተዋል።
ዘግይተው በሚዘሩ እንደ ክንክና ገብስ እና የጥቁር አፈር ጤፍ ሰብሎች ሊሸፈን እንደሚችል ጠቁመዋል። አርሶ አደሮች ማሳቸውን በሰብል እንዲሸፍኑም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በክልሉ አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሎ የታቀደው ግብዓት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለክልሉ እንደተገዛ የገለጹት አቶ አጀበ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ክልሉ የተጓጓዘ መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉ ከከረመው ማዳበሪያ ጋር ተዳምሮ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል። ከዚህም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀርቧል ብለዋል።
ለአገልግሎት ከቀረበው ግብዓት ውስጥም በተከሰተው አለመረጋጋት ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ተናግረዋል።
በተከሰተው የፀጥታ ችግር ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የተጫኑ አሽከርካሪዎች ከተሞች ላይ መቆማቸውን አስረድተዋል።
የግብዓት አቅርቦት ሥራው በሰላም እጦት በሚፈለገው ልክ አለመቅረቡ በምርታማነቱ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፣ በተለይ የበቆሎ ሰብል ያለዩሪያ የሚሠጠው ምርት አናሳ ነው ብለዋል።
ምዕራብ አማራ ሰፊ የግብዓት ጥያቄ ቢኖረውም በተከሰተው ችግር ማድረስ እንዳልተቻለ ያነሱት አቶ አጀበ የሰላሙ ኹኔታ እየተሻሻለ በመጣባቸው አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች መጋዝን ላይ ያለን ግብዓት ለማሰራጨት እየተሞከረ መኾኑንም ጠቁመዋል።
አቶ አጀበ ክልሉ ምርጥ ዘር የመጠቀም ልምድ እንዳለውም አንስተዋል። ለመኸር እርሻው ከ210 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለመጠቀም ታቅዶ እንደነበር የገለጹት ኀላፊው እስካሁን 160 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰራጨቱንም ጠቁመዋል።
ከ11 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ እና ሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ኀላፊው ያነሱት።
ሰብሎችን ከመንከባከብ አንጻር ባነሱት ሃሳብ ምሥራቅ አማራ ላይ በሦስት ዞኖች ውስጥ በ10 ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ጠቁመዋል።
እንዲኹም በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሥንዴ ዋግ በሽታ ላይ ርጭት መካሄዱንም አንስተዋል።
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በመንከባከብ በኩል የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን አንስተዋል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት አረም የማረም፣ የመኮትኮትና የመሳሰሉ ሥራዎች በወቅቱ የተከናወኑ ተግባራት መኾናቸውንም አንስተዋል።
አቶ አጀበ የምርት ማሳደጊያ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ የኾነው የግብዓት አቅርቦቱ ቀድሞውኑም የዘገየ ቢኾንም በተፈጠረው አለመረጋጋት የበለጠ ተስተጓጉሏል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!