
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው መከበራቸውን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ በወረኃ ነሐሴ በአማራ ክልል በርካታ ሃይማታዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡ የቡሔ በዓል (ደብረታቦርን በደብረታቦር)፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንገጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ በክልሉ በድምቀት ይከበራሉ፡፡ በዓላቱ በርካታ ጎብኚዎችን የሚስቡ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና ማንነት የሚገለጽባቸው፣ የሕዝብ ሥነ ልቦና የሚታይባቸው ናቸው፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋት ምክንያት የነሐሴ ጌጦች አይከበሩም የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መሠረታቸውን እንደያዙ፣ ሕዝባዊነታቸውን እንደጠበቁ ተከብረዋል፡፡ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ በወረኃ ነሐሴ በአማራ ክልል በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት እንደሚከበሩ ገልጸዋል፡፡ የቡሔ በዓል ደብረታቦርን በደብረታቦር ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በድምቀት መከበሩንም አስታውሰዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት በሰሜን ወሎና በዋገኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በድምቀት መከበራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በዓላቱ ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ እስካሁን ተከብረውባቸው በማያውቁ አካባቢዎች ዞናዊ ኾነው መከበራቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን አላማጣ ከተማ ከዞኑ የተውጣጡ ልጃገረዶች እና የበዓሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በድምቀት መከበሩንም አስታውቀዋል፡፡ የአደባባይ በዓሉ ከመከበሩ አስቀድሞ የፓናል ውይይት መዘጋጀቱን እና በዓላቱን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸውም ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ባሕላቸውን በነጻነት ለማክበር ይቸገሩ የነበሩ አካባቢዎችም ዘንድሮ በነጻነት፣ በአንድነትና በሰላም ማክበራቸውን ተናግረዋል። በዓሉ በአላማጣ ከተማ በድምቀት መከበሩንም አንስተዋል፡፡ በዓላቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በርካታ ጎብኚዎችን በመሳብ ከቱሪዝም ከሚያስገኙት ገቢ ባለፈ የሚፈጥሩት የገበያ ትስስር ላቅ ያለ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ማኀበራዊ አንድነት እና መግባባት እንዲፈጠር ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት ነጻነትን የሚያመላክቱ የሴቶችን ድርሻ ከፍ የሚያደርጉ ናቸውም ብለዋል፡፡ በጦርነት የተጎዳውን አካባቢ የሚያነቃቁና ወደ ነበረበት የጠነከረ ሥነ ልቦና የሚመልሱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ባሕል ታሪክና ማንነት ነው ያሉት ኀላፊው በተለይም አላማጣና ኮረም አሸንጌ ላይ የተካሄደው በዓል ትልቅ ትርጉም የነበረው መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ሻደይ እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር በኮረም በቅርብ ርቀት በአሸንጌ ሐይቅ መከበሩንም አስታውሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለበት፣ ሌትም ቀንም ጦርነት ያለበት እንደኾነ አድርገው ለሚያስቡና ለሚናገሩ ሰዎች በዓላቱ በሰላማዊ ሁኔታ በድምቀት መከበራቸው ምላሽ የሚሰጥ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል ያለውን የተሳሳተ ዝንባሌ የሚያስተካከል በዓል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዓላቱን በድምቀት ያከበረው ሕዝብ ምስክር ነው ብለዋል፡፡ ቢሮው በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንዲከበሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ቀጣይ የሚካሄዱ በዓላትን በድምቀት ለማክበር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለቱሪዝም የመጀመሪያው ግብዓት ሰላም ነው ያሉት ኀላፊው ቱሪዝም ጥሞናን የሚጠይቅ፣ አንጻራዊ ሰላም ሳይኾን ፍጹም ሰላምን የሚፈልግ ነው ብለዋል፡፡ ፍጹም ሰላም እንዲረጋገጥ ደግሞ መንግሥት ሰፊ ድርሻ ቢኖርበትም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ ሰላም ሲኖር እንግዶች ይመጣሉ፣ እንግዶች ሲመጡ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፣ ምጣኔ ሃብቱን ይደግፋሉም ብለዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያቸውን የመሠረቱ አካባቢዎች ሰላም ሲታጣ በእጅጉ እንደሚጎዱም ገልጸዋል፡፡ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመኾን ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ከጦርነት እና ከብጥብጥ የሚገኘው ውድመት ብቻ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!