
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በብዛት ምርት ከሚገኝበት አካባቢ በመግዛት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ዋጋ እያረጋጉ እንደነበር የማሕበራቱ ሥራ አስኪያጆች ተናግረዋል።
የግሽ ዓባይ ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበር ሥራ አስኪያጅ ምትኩ አያሌው ማኅበሩ በርካታ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ሲያከፋፍል የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት ምርት ቢኖርም ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሶ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ አለመቻሉን ያነሳሉ።
ሸማች ማኅበራት ምርት መግዛት የሚችሉት ከዩኒየኖች ብቻ መኾኑን ያነሱት አቶ ምትኩ ከዩኒየኖች የገዙትን ምርት አከፋፍለው በመጨረሳቸው ማኅበሩ ላይ ምርት አለመኖሩን ይናገራሉ። ዩኒየኖች ከፋብሪካ በማምጣት የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ፋብሪካዎችም ያሉበትን አካባቢ ማኅበረሰብ ለማገልገል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የዓባይ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ቢያድግልኝ መርሻ በበኩላቸው የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሠጡ መኾኑን አንስተዋል። በተፈጠረው አለመረጋጋት ሸማቹ የምርት ፍላጎት ቢያሳይም በቂ ምርት እየቀረበ አለመኾኑንም አንስተዋል። ወጥተው ለመግዛት ቢፈልጉም በቂ ምርት ከነጋዴው ላይ ማግኘት አለመቻላቸውንም ይናገራሉ።
ገበያ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት የቻሉት ቡና እና ምስር ብቻ መኾኑን ሥራ አስኪያጁ አቶ ቢያድግልኝ ይናገራሉ። ኅብረት ሥራ ማኅበራት በጋራ የመሠረቷቸው ዩኒየኖች ምርታቸውን ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኀበራት፣ ለሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሊያከፋፍሉ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማሥፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን አንስተዋል። የፀጥታ ችግር በተለያዩ አካባቢዎች በመኖሩ ምክንያት ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚፈልጉትን ምርት ከሚፈልጉት አካባቢ ማምጣት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ምርት ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ አለመቻል አሁን ለተፈጠረው የምርት እጥረት ምክንያት ነው ብለዋል። በተለይ ለአላስፈላጊ የዋጋ ንረት መከሰት ምክንያቱ የሠላም እጦት፣ የአካባቢዎች አለመረጋጋት፣ ሁከት እና ብጥብጥ መኾኑን ተናገረዋል።
አቶ ጌትነት የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ከፋብሪካዎች ጋር ውይይት መጀመሩ ችግሩን ለመቀልበስ አንዱ መንገድ እንደኾነ አንስተዋል። አንጻራዊ ሰላም ባለበት አካባቢ ምርቶችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ኀላፊው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ችግሩን ለመፍታትም በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። ሰላሙ ወደነበረበት እየተመለሰ በመኾኑ አገልግሎቱ ይስተካከላል ያሉት ኅላፊው ሰላሙ ሙሉ በሙሉ እስኪመለስ ድረስ ትኩረት ተሠጥቶት እንደሚሠራም አቶ ጌትነት ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!