“ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሰረታዊ ምርቶችና አቅርቦቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ በኑሯችን ላይ ጫና ተፈጥሮብናል” የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

54

ጎንደር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሰረታዊ ምርቶችና አቅርቦቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ በኑሮአቸው ላይ ጫና መፈጠሩን የተለያዩ ምርቶችንና ሸቀጦችን ሲሸምቱ ያገኘናቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ነግረናውል።

በሰላም እጦቱ ወቅት የግብይት እንቅስቃሴው ተገድቦ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም ቀድሞ ወደነበረው ሰላማዊ የግብይት ሥርዓት ለመመለስ እድል እንደፈጠረላቸው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በዋጋ ላይ የሚታየው የተጋነነ ጭማሪ ምክንያታዊ ያልሆነና ዜጎችን ለምሬት የሚዳርግ መሆኑን ይገልጻሉ።

ነዋሪዎቹ መንግሥት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ሰበብ በማድረግ ያልተገባ የኑሮ ጫና የሚፈጥሩትን በመቆጣጠርና አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሊያርምና በበላይነት ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ጥጋቡ አዳነ በመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ጫና ማሳደሩን አንስተው ኅብረተሰቡ ምርቶችን በውድ ዋጋ በብዛት በመሸመቱ ለዋጋ ንረቱ መባባስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሙሐመድ ዳውድ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ዕቃዎች ላይ ጭማሪ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው አሁን ላይ ወደ ከተማዋ በበቂ ሁኔታ ምርቶች በመግባታቸው ወደቀደመው ሰላማዊ የግብይት ሁኔታ መመለሱን ይናገራሉ።

የተከሰተውን የገበያ አለመረጋጋት ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የጎንደር ከተማ ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ጸጋየ ገበያውን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ የገበያ አረጋጊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በተሰራው ሥራም ለውጥ መታየት መጀመሩን ተናግረዋል። ገበያውን ለማረጋጋት ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅስው ለ117 ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የመምሪያ ኀላፊው አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፡- መሰረት ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም በሰማይም በምድርም ላሉት ታስፈልጋለች” መምሕር ሐረገወይን በሪሁን
Next article“ ኢትዮጵያ ሰላምና ሰላማውያንን አጥብቃ ትፈልጋለች”