በወገልሳ የተቀናጀ የአሳ ግብርና ኘሮጀክት ላይ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱን ተቋሙ ገለጸ፡፡

54

ባሕር ዳር: ነሃሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሰሜን ጎጃም ዞን የሚገኘው ወገልሳ የተቀናጀ የአሳ ግብርና ኘሮጀክት በሀገር ደረጃ የመጀመሪያው ፕሮጀክት መኾኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ነግረውናል፡፡

ወገልሳ የተቀናጀ የአሳ ግብርና ኘሮጀክት አስተባባሪ እንዳለ ለማ ለአሚኮ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በባለሀብቶች የአሳ ግብርና ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሌለ እና አይን ገላጭ የሚባል ፕሮጀክት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች እና ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ የሚወስዱበት የክልሉ ትልቅ ሀብት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

ብዙ ተመራማሪዎችም የምርምር ሥራ የሚሠሩበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚሠራውን ሥራ አስፍቶ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሀገሪቱ የአሳ ግብርና የስልጠና ማዕከል ስለሌለ የሀገሪቱ ሥልጠና ማዕከል ለማድረግ ታስቦ ሥራዎች እየተሠሩ እንደነበርም ነግረውናል፡፡

አቶ እንዳለ ለማ እንደነገሩን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ንብረቶች፡-

✍️በውጭ ዜጎች የተሠራ እና በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በመጡ እቃዎች የተሠራው የአሳ ጫጩት ማስፈልፈያ

✍️አምስት ኩሬዎች

✍️ቢሮዎች

✍️መጋዘን እና ውስጡ የነበሩ እቃዎች መውደማቸውን እና መዘረፋቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተፈጠረው ችግር ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ ንብረት እንደወደመበትም ነው አቶ እንዳለ ያብራሩት፡፡

በዚህ ተቋም ላይ የደረሰው ጉዳት በአሳ ምርት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ተጽእኖ እንዳደረሰም አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በመውደሙ በአማራ ክልል በአሳ ሙያ ዘርፍ መመራመር ለሚፈልጉ ፣በዘርፉ እየተማሩ ያሉ እና ተሞክሮ መለዋወጥ ለሚፈልጉ ሁሉ የሚፈልጉትን እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ነው አስተባበሪው የተናገሩት፡፡

ፕሮጀክቱ አሁን ከደረሰበት ውድመትም በላይ ሙሉ በሙሉ እንዳይወድም ኅብረተሰቡ ያደረገው ርብርብ የሚደነቅ መኾኑን የገለጹት አቶ እንዳለ ኅብረተሰቡ ንብርቱን በመጠበቁ አመሥግነዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ታቦር ከተማ በሙሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ መኾኗን ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleየሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የአብሮነት እሴቶችን በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ሀገራዊ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡