“የሸቀጥን ዋጋ ከእጥፍ በላይ አንሮ መሸጥ ሞራለቢስነት ነው” ሸማቾች

49

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላምን ዋጋ ለማወቅ መመራመር አያሻም፣ሰላም ሲደፈርስ የሚፈርሰውን ጓዳ ማየት ብቻ በቂ ነው። ሰላም ሲርቅ ከእያንዳንዱ ቀን ጋር የሚመጡ አዳዲስ ችግሮችን መረዳት አይቸግርም።

የሚያመው ግን የሰላሙ ባለቤት የኾነው ፣የችግር ሁሉ የመፍትሔ አካል የሚባልለት እራሱ ሰው አንዱ በአንዱ ላይ የጎደለውን ለመሙላት ሳይኾን የበለጠ ለማጉደል እሽቅድድም ላይ መኾኑን ማየት ነው።

የሰው ልጅ ከሕግና ሥርዓት ብቻም ሳይኾን ከሞራሉ ፣ከስብእናው፣ከማኅበረሰባዊ ወጉ እየጎደለ ሲሄድ ለመፍትሔው እየራቀ ነውና መዘዙን የከፋ ያደርገዋል።

ዶክተር ጠና ደዎ “ሰው፣ግብረገብና ሥነ-ምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች” በሚል ባሳተሙት መጽሐፋቸው ዛሬ ላይ በዓለም የሰው ልጆች የችግር ሰለባነት የግብረገብነትና የሥነ ምግባር ዝቅጠት የወለደው አቅመቢስነት ስለመኾኑ አስነብበውናል።

ዶክተር ጠና ደዎ የሰው አቅመቢስነቱ ደግሞ ከአለመቻል አይደለም ይሉታል። የሰው ልጅ ለችግሮቹ ዕውቀት አላነሰውም፣ለድህነቱም ሀብት አልጎደለውም፣ለችግሩም መፍትሔ አልጠፋበትም አቅመቢስ ያደረገው ፣ ከሰውነቱ ያጎደለው ግብረገብነትና የነጠፈ ሥነምግባር ነው ባይ ናቸው።

ጸሐፊው እንደሚስማሙበት ግብረገብነት ተዳክሞ ስግብግብነት፣እራስ ወዳድነት፣ክፋትና ተንኮል፣ስርቆትና ውሸት፣ቂምና በቀልን አርግዞ እየተወለደ ዓለምን አጎሳቁሏል።

በእርግጥም ማኅበረሰባዊ ችግር ከፍታ ላይ ወጥቶ ሰው ስብእናውን በኪሱ ከትቶ እየተጓዘ ይመስላል።

ለቁስ አዳሪው በዝቷል፣ሰው ሁሉ ከሰው ክብር ይልቅ ሰው የፈጠረውን ቁስ አስበልጧል።

ሰው ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ከመኾን ይልቅ በተንኮል፣አንዱን አንዱ ጠልፎ በመጣል፣ወይም በሌሎች ችግር ላይ ማትረፍን እየተለማመደ መጥቷል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት በንግድ ሥርዓቱ ላይ ከችግር ላይ ሌላ ችግር የሚፈጥሩ ሻጭና ሸማቾችን አሳይቶናል።

የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ከተፈጠረው ቀውስ ለማትረፍ ፣ የምርት እጥረት የተፈጠረ ከማስመሰል እስከ ሐሰተኛ አሉባልታን ማስወራትና ማኅበረሰብን ማደናገር ፣ላልተፈለገ ኪሳራም መዳረግ ተስተውሏል።

” በግጭቱ ምክንያት ምርት ከገበያ ይጠፋል ፣ መንገድ ድጋሜ ይዘጋል ፣ አስቤዛ ሸምቱ ተብሏል” የሚሉና መሠል አደናጋሪ መልዕክቶች ከችግር አትራፊዎች እየተፈበረኩ ወደ ማኅበረሰቡ ጀሮ ሲደርሱ የነበሩ መልዕክቶች ናቸው።

እርግጥ ነው የሚፈጠረው ግጭት አዘቦታዊ እንቅስቃሴን ይገታል ፣ ግጭት በራሱ ችግር ነው፤ ዋጋ ያስከፍላል ፣በግጭቱ ምክንያትም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተግትቶ ምርት እና ሸቀጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ጉዳይ ለጊዜው ይገታል ፣ ይህ ያለ የነበረ የሚኖርም ነው ፣ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ግጭት ተፈጥሯዊ ነውና።

የሚያስተዛዝበው ግን ከችግር አትራፊዎች የሚሰነዘረው እጅ ርዝመት ነው።

ከጥቂት የሞራል ጥጋቸውን ከሚጠብቁ ምስጉን ነጋዴዎች በስተቀር በነጠፈ ስብእና ከሞራልም ከሕግም የሚያፈነግጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ገበያውና ግብይቱ የተመሰቃቀለ እንዲሆን ያደርጉታል።

ኮሽታን ጥግ አድርገው ምርትን በመደበቅ እጥረት ተከስቷል የሚሉ በአማኑ ጊዜ ባለው ዋጋ የሰበሰቡት ምርት ላይ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝብን ለምሬት ፣ እነሱም በአልተገባ መንገድ ለመክበር ሲኳትኑ ሰንብተዋል።

ስግብግብ ነጋዴ ፣ስግብግብ ሸማችንም ፈጥሯል። ምንአልባትም ለሦስት ቀን ችግር የሦስት ወር አስቤዛ የሚሰበስብ ሸማች ታይቷል እንደማለት ነው።

ስግብግብ ነጋዴዎች ያጣን ለብድር ፣የነጣን ለርሃብ ዳርገው የሌላ ችግር ሰለባ ያደርጉታል።

በተፈጠረ ችግር ያለአሳማኝ ምክንያት የሸቀጥን ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ መሸጥ ሞራለቢስነት ነው።

ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ በተነዛ አሉባልታ ገበያው ላይ የታየው ይሄው ነው።

እንደማሳያም በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ “ከነገ ጀምሮ መንገድ ይዘጋል ፣አስቤዛ ሸምቱ ተብሏል” የሚል አሉባልታ የሰማ ሸማች በኪሎ 30 ብር የሚሸጥን ድንች እስከ 90 ብር ሲሸምት ውሏል።

ከ1ሺህ 100 ብር በላይ ያልነበረን የምግብ ዘይት እስከ 1ሺህ 450 ብር ድረስ ፤ አንድ ኪሎ ሽንኩርትን እስከ 150 ብር ድረስ መግዛታቸውን ያነጋገርናቸው የባሕር ዳር ከተማ ሸማቾች ነግረውናል።

የተወራው ኾን ተብሎ መኾኑ ሲረጋገጥ ግን ከአንድ ቀን አዳር በኋላ ግብይቱ መልኩን እየቀየረ ወደ ነበረበት እየተመለሰ መኾኑን ትዝብታቸውን አጋርተውናል።

አምስት ሊትር የምግብ ዘይትም እንደ አይነቱ በአንድ ቀን ከ1ሺህ 450 ብር ወርዶ ከተሸጠበት የ400 ብር ቅናሽ አሳይቷል።

ይህ በምርት አቅርቦትና ፍላጎት ኢ-ተናባቢነት የተፈጠረ የዋጋ ልዩነት አይደለም። ከችግር አትራፊዎች እንጂ ሲሉ ሸማቾች ይተቻሉ።

ከትላንት እና ከዛሬ ነገ ያስፈራል በሚል ማስፈራሪያው ገበያው በምርት እጥረት እንደተራበ ሲያስወራ የዋለው ነጋዴ፣ ያቀደው አልሰምር ሲለው የደበቀውን እያወጣ ለገበያ እያቀረበ ይመስላል። እንደ ሸማቾች ትዝብት ገበያው እንደተፈራው አይደለም ፣ የለም የተባለው ምርት ለሽያጭ እየቀረበ ነው።

እንደምሳሌ ያነሳናቸው መሰረታዊ ሸቀጦች ታሪክ ከሰሞኑ የአብዛኛው የግብይት ውጤት መገለጫ ናቸው።

በሚፈጠሩ እኩይ ድርጊቶች ሁሉ የችግሩ ፈጣሪ ሰው ፣ ሰለባውም ሰው ፣የመፍትሔ አካሉም ሰው መኾኑ ግልጽ ነው።

እናም በየፈርጁ ሰውን ከ”እኩይ ድርጊት ምሽግነቱ” ከሚያስወጣው ግብረገብነት እና ሥነምግባር ግንባታ ላይ መሥራት የችግሮች ሁሉ መውጫ መንገድ ነውና በዚህ ጉዳይ ላይ በትኩረት ቢሰራ መፍትሄው ሩቅ አይሆንም።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦት የምርት አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረትን በማባባስ ኅብረተሰቡን ለችግር ስለሚያጋልጥ ሁሉም ለሰላም ሊሠራ ይገባል” የባሕርዳር ነዋሪዎች
Next articleደብረ ታቦር ከተማ በሙሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ መኾኗን ነዋሪዎች ገለጹ።