
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የአቅመ ደካማ ቤቶች ለነዋሪዎቹ ተላልፈዋል።
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለሀብቶችን በማስተባበር ነው የአቅመ ደካማ ቤቶችን አስገንብቶ ያስረከበው።
ቤቶችን የገነቡት ባለሀብቶች ባለይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ፣ ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ ብዙዓለም ኪድስ፣ ሪች ላንድ እና ሙሉጌታ መኮንን መኾናቸውም ተገልጿል።
በከተማዋ ግንባታቸው ከተጀመሩ 57 ቤቶች አብዛኛዎቹ ተጠናቅቀው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል። ቀሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቀው እንደሚተላለፉ ነው የተመላከተው።
የቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራዎችን ድርጅት የፕሮጀክት ክትትልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው እንዳላማው በፍኖተ ሰላም ከተማ በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት 12 መኖሪያ ቤቶችን ሠርተው ማስረከባቸውንም ገልጸዋል። ቤቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸውም ተናግረዋል። ቤአኤካ በማኅበራዊ አገልግሎት በስፋት እየተሳተፈ መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የክልሉን ሕዝብ የማገልገል ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።
በሌሎች ከተሞችም የአቅመ ደካማ ቤቶችን ግንባታ እንደሚገነቡ ነው የገለጹት። ከአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ ባለፈ በሌሎች ዘርፎች ለማኅበረሰብ በሚጠቅሙ ሥራዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። ሌሎች ባለሀብቶችም ከቤአኤካ ተሞክሮ በመውሰድ ማኀበራዊ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት። ድርጅታቸው ለማኅበራዊ አገልግሎት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥና የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በፈለጋቸው ጊዜ ደራሽ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን የንግድና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሀብቶችን በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን ቤቶች እያስገነባ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የአቅመ ደካማ ቤቶቹ ለመኖሪያ የማይመቹ አስቸጋሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ባለሀብቶችን እያስተባበረ ድጋፍ እያደረገ እያሠራ መኾኑም ተናግረዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የትብብር ባሕል እያደገ እንዲሄድ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ትብብር እና በጎ አድራጎት ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!