
እንጅባራ: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዳንግላ ከተማ አሥተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 31የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ፣የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ፣ የወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ሸዶች፣የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የቢሮ ግንባታና መለስተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥልቅ ጉድጓዶች ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት ከበቁ መሠረተ ልማቶች መካከል ይገኙበታል።
ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ ከዓለም ባንክ፣ከክልሉ መንግሥት ድጋፍና ከኀብረተሰቡ ተሳትፎ የተገኘ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል።
የዳንግላ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሙሉቀን በዙ የተጠናቀቀው በበጀት ዓመት የመንግሥት፣የልማት አጋር ድርጅቶችንና የኀብረተሰቡን አቅም አቀናጅቶ በመጠቀም የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት እንደነበር ገልጸዋል።
የተገነቡ መሠረተ ልማቶች የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑና የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጨምሩ መኾናቸውንም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው ግንባታቸው ተጠናቀው የተመረቁ መሠረተ ልማቶች በችግሮች ሳንወሰን የኀብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማንታክት መኾናችንን ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የከተሞችን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ለልማት ማነቆ የኾኑ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን እና ሥርዓት አልበኝነትን መታገል ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኀብረተሰቡ ለሠላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዳንግላ ከተማ ነዋሪዎችም የተገነቡ መሠረተ ልማቶች የነዋሪዎችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያቃልሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለመሠረተ ልማቶች ግንባታ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ሲደግፉ መቆየታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እንክብካቤ እንደሚያደርጉላቸውም ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያም በመሠረተ ልማት ግንባታ ወቅት አስተዋጽዖ ለነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!