
ከሚሴ: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ 99 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው 23 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የከሚሴ ከተማ ከንቲባ ከድጃ አሊ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ፣በዓለም ባንክና በኀብረተሰቡ ትብብር ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 1 ሺህ 893 ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሱለይማን እሸቱ ገልጸዋል።
ከነዚህ መካከል 850 ያህሉ በኀብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ ናቸው ያሉት አቶ ሱለይማን ለግንባታውም 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መኾናቸውን ያነሱት የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ ኀብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ሰላም ወሳኝ ሚና ስላለው ሁላችንም ለሰላም መስፈን የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በከተማው የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከዚህ በፊት ይገጥማቸው የነበረውን ችግር የሚቀርፉ መኾናቸውን አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በፕሮጀክቶቹ ምርቃ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!