
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንቨስትመንቱን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እንዳነቃቃው ተገልጿል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት፤ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው አኳያ ምርታማ የኢንዱስትሪ ተቋማትን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት 865 አዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ እንድሪስ ወደ ምርት ከገቡት ኢንዱስትሪዎች 322 የሚሆኑት የአምራች ኢንዱስትሪዎች መኾናቸውን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ 543 የሚኾኑት ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በበጀት ዓመቱ ወደ ምርት ከገቡት ኢንዱስትሪዎች 63 ሺህ 432 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት አቶ እንድሪስ፤ ንቅናቄው የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው በ20ሺ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ የንቅናቄው አንዱ ዓላማ አዳዲስ ተቋማት ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ በመሆኑ በክልሉ አዳዲስ እና ምርት ያቆሙ ተቋማት ወደ ምርት ገብተዋል። በኢትዮጵያ ታምርት በባለሀብቶች ሲነሱ የነበሩ የአሠራር፣ የግብዓትና የኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለማሻሻል የኢንቨስትመንት ቦርድ ደንብን ከማሻሻል ጀምሮ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት ጥረት ተደርጓል።
በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንድ ሚሊዮን 675 ሺህ 218 ቶን ተኪ ምርቶችን በማምረት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ38 በላይ ኢንዱስትሪዎች በበጀት ዓመቱ ከ80ሺ ቶን በላይ ምርት በማምረት ወደ ውጭ የተላከ መሆኑን አመልክተው፤ከአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በአጠቃላይ 138 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደተገኘ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት መንግሥት ቀደም ሲል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያወጣ ሲያስገባቸው የነበሩ ምርቶችን 401 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት በመግባታቸው አንድ ሚሊዮን 675 ሺህ 218 ቶን ተኪ ምርቶችን በክልሉ ማምረት መቻሉን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህም አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን መግለጻቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!