
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት 483 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አራት ሺህ 724 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት፤ ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 483 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አራት ሺህ 724 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ሰጥቷል። ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡም ከ957 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፤ አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከተሰጣቸው ዘርፎች ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ድርሻ የሚይዘው የማኑፋቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው።
32 ሺህ 157 ሄክታር መሬት ለአንድ ሺህ 288 ባለሀብቶች መተላለፉን ገልጸው፤ ለባለሀብቶቹ ከተላለፈው መሬት ውስጥ አንድ ሺህ 477 ሄክታር መሬት በላይ የሚሆነው ለአምራች ኢንዱስትሪው መተላለፉንና ቀሪው ለሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተላለፈ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ተከታታይ ድጋፍ እና ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ እንድሪስ፤ በውላቸው መሰረት ወደ ልማት በማይገቡት ኢንቨስተሮች ላይ ግን በየደረጃው ባሉ አካላት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና 127 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሬታቸው መነጠቁን ገልጸዋል።
ሚዲያዎች ክልሉን በማስተዋወቅ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ እንዲመጡ ለሚጫወቱት ትልቅ ሚና አቶ እንድሪስ ምስጋና አቅርበዋል። ክልሉ በጣም ሰፊ የጸጋዎች ምድር በመሆኑ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!