በፍኖተ ሰላም ከተማ በ157 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች እየተመረቁ ነው።

32

ፍኖተ ሰላም : ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር በ157 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ተጠናቅቀው እየተመረቁ ነው።

መሠረተ ልማቶቹ የተገነቡት በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደርና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ነው። ዛሬ እየተመረቁ የሚገኙት መሠረተ ልማቶች የሕዝብ ቤተ መፃሕፍት፣ ጤና ኬላዎች፣ ድልድይ፣ የጌጠኛ መንገድ ፣ የጠጠር መንገድ እና ሌሎች ናቸው።

በከተማዋ በባለሀብቶች የተገነቡ የአቅመ ደካማ ቤቶችም ተጠናቅቀው ለነዋሪዎቹ እየተላለፉ ነው።

የከተማዋ ነዋሪ ፈንታ እንዳየን በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ችግር እንደነበረ ተናግረዋል። ከአሁን በፊት በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እየተሠሩ የሕዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን መመለስ ከጠቀሜታቸው ባሻገር ለከተማዋ ውበት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለፈ የቤተ መፃሕፍት በመገንባቱ ወጣቶች በዕውቀት እንዲታነጹ እንሚያደርግም ተናግረዋል። ሕዝብ ጥሩና ትጉህ መሪ ካገኘ ለልማት የማይነሳና ልማትን የማያግዝ እንደሌለም ገልጸዋል አቶ ፈንታ። የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሕዝብ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ሙሉ ምትኩ ከዚህ ቀደም የመሠረተ ልማት ችግሮች በመኖራቸው ለችግር ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥያቄዎች እየተመለሱ፣ ማኅበረሰቡም በባለቤትነት መሠረተ ልማቶችን እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት። በከተማዋ የተገነባው ቤተ መፃሕፍት ለልጆቻቸው መልካም አጋጣሚ ይዞላቸው እንደመጣም ተናግረዋል። መሠረተ ልማቶችን የኔ ናቸው ብሎ መንከባከብ እና መጠበቅ ይገባልም ብለዋል። ሁሉም ለከተማው፣ ለአካባቢው እና ለሀገሩ ማበርከት የሚገባውን ማበርከት አለበት፣ ሀገር የምትገነባው ሁሉም በሚያደርገው አስተዋጽዖ ነው ብለዋል ወይዘሮ ሙሉ። ሁሉንም ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴዔታ እንዳለው መኮንን፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ መልካሙ ተሾመ፣ የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ልየው አንሙትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበላይነህ ክንዴ ፋንውዴሽን በፍኖተ ሰላም ከተማ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለኾኑ ወገኖች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ።
Next articleበአማራ ክልል ከ483 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ።