በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሠረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

29

እንጅባራ: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 34 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ፣ የወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ሸዶች፣የመንገድ ዳር መብራትና የጠጠር መንገድ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት መሠረተ ልማቶች መካከል ናቸው ።

ፕሮጀክቶቹ ከዓለም ባንክ፣ከክልሉ መንግሥት ድጋፍና ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ በተገኘ ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።

መሠረተ ልማቶቹን መርቀው የከፈቱት የአማራ ክልል ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢያዝን እንኳሆነ ከተሞችን ለማሳደግ በየአካባቢው ያሉ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ቢሮው እንጅባራ ከተማን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በገንዘብ፣በአይነት እና በዕውቀት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ማቃለልና የኮንስትራክሽን ዘርፉን ማዘመን ቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ -ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ግዛቸው አጠና በበጀት ዓመቱ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጨምሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመንግሥት፣የልማት አጋር ድርጅቶችንና የኅብረተሰቡን አቅም አቀናጅቶ በመጠቀም የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባው ገልጸዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ለመሠረተ ልማት ግንባታው ያሳዩትን አጋርነት መሠረተ ልማቶቹ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ደህንነታቸውን በመጠበቅ ሊደግሙት እንደሚገባም ከንቲባው አሳስበዋል።

የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማዋ የሚስተዋለው የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግር በነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት መሠረተ ልማቶች የነዋሪዎችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚፈቱ ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ የመሠረተ ልማት ግንባታው ከከተማዋ ዕድገት ጋር እኩል መራመድ እንዳለበትም አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ተገንብተው ለአገልግሎት ለበቁ መሠረተ ልማቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመጠቆም በቀጣይም የከተማዋን የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ለመሠረተ ልማት ግንባታው ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዕውቀታችሁን ወደተግባር በመለወጥ ታሪካዊ ኀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል” የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ከፍያለው አለማየሁ
Next articleደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው።