“መንገድ እና ንጹህ መጠጥ ውኃ የክልላችን ሕዝብ የዘወትር ጥያቄዎች በመኾናቸው ምላሽ ለመሥጠት ሳንታክት እንሠራለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

60

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) የምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ እና ተጨማሪ ማብራሪያ እየሰጡ ነው። ከተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብን የወከሉ የምክር ቤት አባላት የመንገድ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት መጓደልን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በጉባዔው ላይ አንስተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩም የቀረቡት ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸው ስለመኾኑ ገልጸዋል። የመጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለመቅረፍ በርካታ ትላልቅ የውኃ ፕሮጀክቶች ቢገነቡም የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ከማርካት አኳያ ግን ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ጎንደርን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ የክልሉ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ያለባቸው ስለመኾኑ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሩ በዘላቂነት ተፈትቶ ሕዝቡም እፎይታ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከመንገድ አኳያም በዚህ ዓመት በርካታ ድልድዮች እና ተንጠልጣይ ድልድዮች በክልሉ አቅም ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ተናግረዋል። በፌደራል እና በክልል መንግሥት ተይዘው የሚሠሩ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጊዜ ከመጠናቀቅ አኳያ ግን ውስንነቶች አሉ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል። የተጀመሩ መንገዶች በፍጥነት ተጠናቅቀው የክልሉን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመኾን በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ “መንገድ እና ንጹህ መጠጥ ውኃ የክልላችን ሕዝብ የዘወትር ጥያቄዎች በመኾናቸው ምላሽ ለመሥጠት ሳንታክት እንሠራለን” ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዜጎችን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በትኩረት ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next article“በፈታኝ ችግር ውስጥም ኾነን በክልሉ የተፈጠረው የሥራ እድል አበረታች ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)