“ዜጎችን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በትኩረት ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

57

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።

በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ለሚገኘው ሕዝብ ምን መፍትሔ ተበጅቷል፣ እንዴትስ ሕዝቡን ከችግር ማውጣት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ርእሰ መሥተዳድሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሸቀጦች የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት፣ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ተዳምረው ሕዝቡን ለምሬት እየዳረጉት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታው በፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግር፣ ሕዝባችን በልቶ በማደር ሁኔታ እየተፈተነ ነው ብለዋል።

ለተፈጠረው ችግር አስፈላጊውን መፍትሔ ማስቀመጥ ላይ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።

የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አምራችነት ላይ በስፋት መሥራት፣ ባሉት ምርቶችም የሚታየውን የፍትሐዊነት ችግር መከላከል፣ የሸማች ኅበረት ሥራ ማኅበራትን ማስፋፋት፣ መደገፍና ማጠናከር ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለመንግሥት ሠራተኛው በየተቋማቱ በዋጋ ቅናሽ የሚያቀርቡበት ሥርዓት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴንና ኮንትሮ ባንድን መከላከል ለንግድ ቢሮ ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።

ግብርናን ማዘመን፣ አምራችነትን ማስፋት የተፈጠረውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለመመከት በሚያስችል ደረጃ የሚሠራበት ነው ብለዋል።

“ዜጎችን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በትኩረት ይሠራል” ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል።

ማኅበረሰቡ የኑሮ ውድነቱ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመቋቋም የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባሕሉን መጠቀም እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ በወቅቱ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) ገለጹ።
Next article“መንገድ እና ንጹህ መጠጥ ውኃ የክልላችን ሕዝብ የዘወትር ጥያቄዎች በመኾናቸው ምላሽ ለመሥጠት ሳንታክት እንሠራለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)