የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሥራ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡

49

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ‹‹አልማን እደግፋለሁ፤ የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እሮጣለሁ›› የአልማ ሳምንት መርሐ ግብር ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሔደ ይገኛል፡፡ መርሐ ግብሩ እስከ ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም ይቀጥላል፡፡

የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አላማና ግብ ለማስተዋወቅ ከተዘጋጁ መርሐ ግብሮች ውስጥ ስፖርታዊ ውድድሮች ይገኙበታል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣትና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አብርሃም አሰፋ ባሕር ዳር ለስፖርታዊ ውድድር ተመራጭ ከተማ እንደኾነች ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታትም የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት የክልሉን ልማት መደገፍና የከተማዋን የገጽታ ግንባታ ሥራ መሥራት መቻሉን አንስተዋል፡፡

የአማራ ልማት ማኅበር በክልሉ እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን ለማጠናከር መምሪያው ከልማት ማኅበሩ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄዱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በዚህ ዓመትም የማኅበሩን አላማዎች ለማሳካት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የፊታችን እሑድ እስከ 2 ሺህ 500 ሰዎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድም አስረድተዋል፡፡

የስፖርት ማኅበረሰቡ ጤናውን በመጠበቅ የአልማን አላማ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ልማት ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ አለማየሁ ሞገስ እንዳሉት አልማ ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ በክልሉ በትምህርት፣ በጤናና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡

ማኅበረሰቡን ከሚያሳትፍባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ስፖርታዊ ውድድሮች ስለመኾናቸው አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት አልማ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣትና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ባካሔዳቸው ስፖርታዊ ውድድሮች የአባላት ቁጥር እያደገ መምጣቱን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ የአልማ ሳምንት በማዘጋጀት የልማት ማኅበሩን አላማና ግቦች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥ ከ41 በመቶ በላይ ምክንያቱ ከወሰን ማስከበርና ከመሠረተ ልማት ችግር ጋር የተያያዘ ነው” ኤሌክትሪክ አገልግሎት
Next article“የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ልጆችን ችግር ለመቅረፍ እንሠራለን” የአማራ ክልል የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ማኅበር አባላት