ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 75 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ።

100

አዲስ አበባ: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት የገቢ ምንጮችን በማስፋት፣ በዋናነት ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር ያሉ በርካታ ተቋማትና አጠቃላይ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ የዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክና የሲስተም አቅም በማሳደግ 75 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አግኝቷል፡፡

ድርጅቱ ከዕቅዱ 101 በመቶ ማሳካቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬህይዎት ታምሩ ገልጸዋል።

ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ23 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።

የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 43 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ዳታና ኢንተርኔት 26 ነጥብ 6 በመቶ፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9 በመቶ፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 6 ነጥብ 9 በመቶ፣ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሣሪያዎች (ቀፎ፣ ዶንግል፣ ሞደም) 4 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ አላቸው ብለዋል ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ።

የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች ማለትም ዓለም አቀፍ ኢንተርኮኔክት፣ ሮሚንግ፣ ከመሠረተ ልማት ኪራይ እና ከሀዋላ አገልግሎቶች አጠቃላይ 164 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ችሏል፡፡ አፈጻጸሙም 107 ነጥብ 8 በመቶ ነው ብለዋል።

የገቢ ዕድገቱ የተመዘገበው በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የተስተናገደው የትራፊክ መጠን በመጨመሩ ሲኾን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በድምጽ ትራፊክ የ34 ነጥብ 5 በመቶ እና በዳታ ትራፊክ የ94 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ተብሏል።

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ገቢን በማሳደግ፣ ወጪ ቆጣቢ አሠራርና ባሕልን በማስረጽ እንዲሁም ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት 51 ነጥብ 2 በመቶ ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡

ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ያልተጣራ ትርፍ መጠን በ24 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

ከተያዘው ዕቅድ አንጻርም 135 በመቶ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገበ ስለመኾኑ ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ አስገንዝበዋል።

ቴሌ በበጀት ዓመቱ የአገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቹን ብዛት 72 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ማጠናቀቂያ ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ከዕቅድ አንጻር የ98 በመቶ አፈጻጸምም አስመዝግቧል፡፡

በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 69 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ 618 ነጥብ 3 ሺህ፣ የመደበኛ ስልh ደንበኞች 853 ነጥብ 6 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 33 ነጥብ 9 ሚሊዮን ናቸው ተብሏል።

አሁን ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም ላይ ካሉ 774 ኦፕሬተሮች መካከል በሞባይል ደንበኛ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ የያዘ ሲኾን በዓለም 21ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሴቶች ውሳኔ ሰጪ ቦታ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ አለብን” ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
Next article“ዳያስፖራው በሀገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከተ ያለውን በጎ አስተዋጽዖ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ