የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ክዋኔውን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ከማስተላለፍ ባሻገር የኢኮኖሚ ተጠቃነሚትን እንደሚያሳደግ ተገለጸ::

352

የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ክዋኔውን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ከማስተላለፍ ባሻገር የኢኮኖሚ ተጠቃነሚትን እንደሚያሳደግ ተገለጸ::

የዓለም የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) በ1946 (እ.አ.አ) ሲቋቋም ተቀዳሚ ዓላማው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮፓ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍትን፣ ሙዚየሞችን መልሶ ለመገንባት በማለም ነበር፡፡ 193 የዓለም አገራትን በአባልነት ያቀፈውና መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው የዓለም የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከእነዚም መካከል በባሕልና ቅርስ ዘርፍ ዓለማችን ያሏትን ሀብቶች ጠብቃ ለትውልድ እንድታስተላለፍ ጥበቃም እንዲደረግላቸው በማለም በየጊዜው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶችን በዓለም ቅርስነት መዝገብ ሲያሰፍር ቆይቷል፡፡ ይህንን ተግባር ለማከናወን አባል ሀገራቱ ባወጧቸው መመዘኛዎች መሠረት ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት ከተደረገ በኋላ በምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ቅርሱ በዓለም ቅርስነት ይመዘገባል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች መነሻ በማድረግ ከአፍሪካ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ትሰለፋለች፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊነቱ ባለፈ በቱሪስት መስህብነቱ የሚታወቀው የጥምቀት በዓል በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ መስፈሩን ተከትሎ ያነጋገርናቸዉ የዘርፉ ምሁራን አስተያዬታቸውን ሰጥተውናል፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ሆቴል የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አያና ፍስሐ የጥምቀት በዓል በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ቅርስነት መመዝገቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ የጥምቀት በዓል የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ የሚታወቅ ሃይማኖታዊ ሁነቱን እንደጠበቀ የቆየና በዓለም ቅርስነት ከመመዝገቡም ቀደም ብሎ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እያደገ የመጣ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ አቶ አያና ጥምቀት በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በዓለም ዙሪያ በስፋት እንዲታወቅ ከትልልቅ ሆቴሎች ጀምሮ እስከ አነስተኛ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የቱሪስቱን ፍሰት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ምዝገባው ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባለፈ ኅብረተሰቡ ትውፊቱን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፍና የጠነከረ ማኅበራዊ ትስስር እንዲኖር በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ የሚመጣውን የዓለም ዕውቅና አስጠብቆ ለማዝለቅ ይቻል ዘንድ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክዋኔውን ሳይበርዝ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ከመጤ የባሕል ወረራ ራሱን እንዲጠብቅና የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሉን አጉልቶ ለዓለም በማሳየት የቱሪስት እንቅስቃሴውን ከወከባ፣ ስርቆት፣ ዝርፊያና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች እንዲከላከል ጭምር አሳስበዋል፡፡

በአበክመ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ስለሽ ፈቃዴ ደግሞ ‹‹የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ጎልታ እንድትታወቅ ከማድረግ ባለፈ የበርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ቀልብ መሳብ እንድትችል ያደርጋል›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን፣ የአክሱም ሃውልትን፣ የጎንደር አብያ መንግሥታትን፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆን፣ የጢያ ትክል ድንጋዮችን፣ የሀረር ጀጎል ግንብና የኮንሶ ባሕላዊ እርከንን በዓለም የሚዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ አስመዝግባለች፡፡ በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ ደግሞ የመስቀል በዓል፣ ፍቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ተመዝግበው ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ የጥምቀት በዓል አከባበር አራተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እንዲሁም በልዩ የተፈጥሮ ጥብቅ ስፍራዎች መዝገብ ውስጥ ደግሞ የጣና ሐይቅ፣ የከፋ ደን፣ የሸካ ደን፣ የያዩ ደንና የማጃንግ ደንን በዓለም ቅርስነት መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር ማድረጓ ይታወቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ኑርሁሴን ሙሐመድ

Previous articleበናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አቋሞችን መከተል አለባት?
Next article“ድርጅቱ ባለብዙ ቋንቋና ከፍ ያለ የሚዲያ ተቋም ነው” የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የቋንቋዎች ዳይሬክቶሬት