
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የብቸና ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ይበልጣል ባይህ የተገነቡ የመሠረተ ልማቶች ለረጅም ጊዜ ማገልገል ይችሉ ዘንድ ኀብረተሰቡ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጥቅሉ 25 ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ሰብለወንጌል ዳኘ በዞኑ በመንግሥት፣ በኀብረተሰብ ተሳትፎና በዓለም ባንክ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜና የጥራት ልክ ተገንብተው ለኀብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ኀብረተሰቡን በማሳተፍ የከተሞችን መሠረተ ልማት ለማሳደግና ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ አስረድተዋል መምሪያ ኀላፊዋ።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ በምክትል ቢሮ ኀላፊ ማዕረግ የቢሮው ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አላምር አንተነህ የብቸና ከተማ አሥተዳደር ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ የገነባቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉን ሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስና ከተሞችን ፅዱና ውብ እንዲሁም ለነዋሪዎች የሚመቹ ለማድረግ ቢሮው በትኩረት እና በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም አቶ አላምር አንስተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት በ98 ሚሊዮን ብር በላይ ግንባታቸው ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት የኾኑ ለወጣቶች የሚተላለፉ ሸዶች ፣ የውኃ መፋሰሻ ዲቾች ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመንገድ መብራት ዝርጋታ፣ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ፣ የደረቅ ጭነት መኪናዎች ማቆሚያና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ናቸው።
ዘጋቢ:- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!