የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ።

127

👉 ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት አጓጉዟል።

ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት 3 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ 2 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ጭነትና 124 ሺ መንገደኞችንም ማጓጓዙንም ገልጿል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ቺፍ ኮርፖሬት ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ አሚኑ ጁሐር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አክሲዮን ማኅበሩ ከአገልግሎት የሚያመነጨው የገቢ መጠን በየዓመቱ በአማካይ የ35 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ነው፡፡

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመትም ብር 3 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የአገልግሎት ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ጭነት ትራንስፖርቱ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ማደግና መኪናን ጨምሮ አዳዲስ ምርቶች በባቡር መጓጓዛቸው ለገቢው መጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውንም አቶ አሚኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ጭነት አጓጉዟል ያሉት አቶ አሚኑ፤ ካለፈው ዓመት ጭነት የ300 ሺ ቶን ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የወጭ-ገቢ የጭነት መጠን 14 በመቶ እንደሚሸፍን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በየቀኑ በአማካይ 500 ተጓዦችን ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ማጓጓዝ እንደተቻለ ጠቁመው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጥቅሉ 124 ሺ መንገደኞችን ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች አጓጉዟል፡፡ ይህም የዕቅዱን 73 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ለሀገሪቷ ወሳኝ የሚባሉ ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በፍጥነት እና በብዛት በማጓጓዝ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በአንድ የባቡር ምልልስ ብቻ ከ2 ሺ 500 ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ በማንሳት ወደ ሀገር ውስጥ አጓጉዟል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት በጥቅሉ 100 ሺህ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በባቡር መጓጓዙን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ገበያ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ከፍተኛ የምግብ ዘይት እጥረት ለመቅረፍ 60 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ በባቡር መጓጓዙን ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በጅቡቲ ወደቦች ይከሰት የነበረን የኮንቴይነር ክምችትና ይህንንም ተከትሎ ይመጣ የነበረ የዴመሬጅ ክፍያን በማስቀረት ረገድ ባቡሩ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየቀኑ በአማካይ 200 ባለ ሃያ ጫማ ኮንቴይነሮችን እያጓጓዘ ነው፡፡

እነዚህን ጭነቶች በባቡር በማጓጓዝ በመኪና ቢጓጓዙ ይወጣ የነበረን የነዳጅ ወጪ በመቀነስ፣ ይፈጠር የነበረን የመንገድ መጨናነቅ እና ወደ ከባቢ ይለቀቅ የነበረን በካይ ጋዝ በማስቀረት ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ኢኮኖሚው ላይ እያበረከተ ካለው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ባሻገር በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ከማጠናከር እና ቀጠናዊ ትስስርን በመፍጠር ሂደት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በተቋሙ በተከናወኑ የሪፎርም እና የአደረጃጀት ማሻሻያ ሥራዎች ተቋሙን ይገጥሙ የነበሩ የተለያዩ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመፍታትና የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት አቅሙን ለማሻሻል መቻሉ ለውጤታማነቱ እገዛ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት እየተከናወነ ነው።
Next articleየአማራ ፖሊስ ኮሌጅ የመደበኛ ፖሊስ አባላትን እያስመረቀ ነው።