
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጤናው ዘርፍ የዲጅታል ክፍያ ሥርዓትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
በጤና ሚኒስቴር የዲጅታል ጤና ክፍል ኃላፊ አቶ ገመቺስ መልካሙ እንዳሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚገኙ የጤና ተቋማት የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት እየተተገበረ ይገኛል። ይህንን መልካም ጅማሮ በማስፋፋት በሌሎች ከተሞችና በገጠራማ አካባቢ በሚገኙ የጤና ኬላዎችም ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ይህንን ሥርዓት በተናበበ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር እየሠራ ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴር እስካሁን በ7 ሺ 800 የጤና ኬላዎች ላይ የራሱን የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ ይህንን የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት እንደ ቴሌ ብርና መሰል የዲጅታል ክፍያ አገልግሎት ከሚሰጡ ጋር በተናበበ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ተገልጋዮች በየጤና ተቋማቱ ክፍያዎችን ሲፈጽሙ የነበሩት እጅ በእጅ ነበር ያሉት አቶ ገመቺስ፣ በአሁኑ ወቅት ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ድረስ ተጀምረው የነበሩ በቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚከናወኑ ክፍያዎችን ወደ አዲስ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት የማስገባት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ይህ ተግባር ከተጠናቀቀ በኋላም ማንኛውም ተገልጋይ ወደ ጤና ተቋማት አገልግሎት ፈልጎ ሲመጣ የተለያዩ የዲጅታል ክፍያ አማራጮችን በመጠቀም እንዲከፈል ይደረጋል ብለዋል።
አዲሱ የዲጅታል የክፍያ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግም በተገልጋዩ ረገድ ለክፍያ የሚባክን ጊዜን የሚቆጥብና ስርቆትን የሚከላከል መሆኑን ጠቁመው፤ በጤና ተቋማት ረገድም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም ሁሉንም ክፍያ ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማስገባት እንደሚሰራ አመልክተው፤ይህም በአጠቃላይ በዲጅታል ሥርዓት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚጠቅም ይሆናል ብለዋል።ዘገባው የኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!