
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ጦርነት በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ቤት ንብረታቸው ወድሟል።
የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዛሬ በደሴ ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ ገጠር ቀበሌዎች እና በከተማዋ ውስጥ ቤታቸው ለወደመባቸው 113 ወገኖች የቆርቆሮ እና ሚስማር ድጋፍ አድርጓል።
በጦርነቱ ወቅት በቤትና አካላቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለአሚኮ የተናገሩት ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች ድጋፉ ቤታቸውን መልሰው እዲሠሩ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እና አቅመ ደካሞችን በመለየት ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ሰይድ ካሳው 4 ሺህ ቆርቆሮ እና 560 ካርቶን ሚስማር መሰጠቱን አስገንዝበዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ በክረምቱ ወጣቶችን በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን እና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለማገዝ እየሠራ መኾኑን ኅላፊው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡- ሳልሃዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!