
ደብረታቦር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ አሥተዳደር ውስጥ በ2015 በጀት ዓመት በ73 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመርቀዋል። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ቢያዝን እንኳሆነ እና ሌሎች የክልል እና የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ከተሠሩት መሰረተ ልማቶች መካከል የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የጠጠር መንገድ፣ የወጣቶች ሥራ መፍጠሪያ ሸዶች፣ የውኃ ማፋሰሻ ቦዮች እና የወጣቶች ሁለገብ ማዕከል ግንባታ ይገኙበታል።
የወረታ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ብርሃኑ ያዜ ከተማዋ በ1941 ዓ.ም እንደተመሰረተች ገልጸዋል። ከ1950ዎቹ ጀምሮ የማዘጋጃ አገልግሎት የተጀመረባት ሲኾን በ1999 ዓ.ም ደግሞ ወደ ከተማ አሥተዳደርነት አድጋለች። ወረታ ከተማ አሁን ላይ የ120 ሺህ ሕዝብ መኖሪያ ስትኾን የወረታ ደረቅ ወደብን ጨምሮ የተለያዩ የልማት አውታሮችን የያዘች ከተማ ናት ብለዋል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከተማዋ በዓለም ባንክ ፕሮጀክት የታቀፈች በመኾኑ የከተማ መሰረተ ልማቶች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በ2015 ዓ.ም 73 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎ የጌጠኛ ድንጋይ፣ የጠጠር መንገድ፣ የሥራ መፍጠሪያ ሸዶችና የውኃ ማፋሰሻ ቦዮች መገንባታቸውን ተናግረዋል። ከአጠቃላይ ወጭው ዓለም ባንክ የደገፈው 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መኾኑን ጠቅሰዋል። ይህ የሚያሳየው መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ከዓለም ባንክ የሚገኘው በጀት እንደማነቃቂያ ይሁን እንጅ ዋነኛው የገንዘብ ምንጭ የከተማ አሥተዳደሩ የራስ ገቢ እና የነዋሪዎቿ ርብርብ መኾኑን ከንቲባው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ቢያዝን እንኳኾነ የዓለም ባንክ ደጋፊያችን ሲኾን ዋነኛ የመሰረተ ልማት ሞተራችን ግን ሕዝባችን ነው ብለዋል። በወረታ ከተማ በ2015 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የላቀ ወጭ የተሠሩ መሰረተ ልማቶችም “የራሳችን አቅም ዋና አንቀሳቃሻችን፣ ዓለም ባንክ ደግሞ ደጋፊያችን” መኾኑን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በጊዜ ተጀምረው በክረምቱ መግቢያ ላይ በመመረቅ ለአገልግሎት መብቃታቸው የከተማዋን ፈጣን የፕሮጀክት አፈጻጸም ተምሳሌት ያደርጋታል ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው በክልሉ የከተሞችን መስፋፋት የሚመጥን መሰረተ ልማት ለመገንባት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አመላክተዋል። የከተሞች መስፋፋት ይዞት የሚመጣውን እድል እና ፈተና ቀድመን በመረዳት በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሁላችንም ከተሜነት እንዲስፋፋ እንደመፈለጋችን መጠን የከተሞች መስፋፋት ይዞት የሚመጣውን ፈተና መቋቋም እና ማለፍም ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ሁሉ የከተማ ነዋሪዎች በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በጉልበት እና በዕውቀት የሚያደርጉት ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት የበለጠ እንዲያድግ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም አቶ ቢያዝን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!