“በዘንድሮው ዓመት 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተገዝቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

51

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና በ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ከምክር ቤት አባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የማዳበሪያ ችግር ለመፍታት እየተሠራ ያለውን ሥራ እንዲያብራሩ በምክር ቤት አባላት ተጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳሉት የማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም በሩሲያና እና በዩክሬን መካከል የተፈጠረው የሰላም ችግር ግዥውን አዘግይቶታል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ለውጡ እንደመጣ ዓመት አካባቢ 450 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ በኾነ ወጭ ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግስት ለማዳበሪያ ግዥ ባደረገው ልዩ ትኩረት 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ዘንድሮ 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተገዝቷል፡፡ ለትግራይ ክልል 800 ሺህ ኩንታል ግዥ መጨመሩንም አብራርተዋል፡፡ አምና ከተረፈው ማዳበሪያ ጋር ተጨምሮ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ መገዛቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ባለው ከ9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ገብቷል ብለዋል፡፡ ቀሪው በመግባት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገር ውስጥ 178 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

በመላ ሀገሪቱ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ ሄክታር መሬት አሲዳማ መኾኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ለማከም ወደ አምስት የሚጠጉ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው የኖራ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ምርታማነት ለመጨመር መሬት ማስፋት ግዴታ መኾኑም አመላክተዋል፡፡ አሁን የተፈጠረውን የማዳበሪያ እጥረት ለመፍታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማስፋፋት ማዘጋጀት ፤አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም ፤ያለውን ማዳበሪያ ፍትሐዊ በኾነ መንገድ በማከፋፈል እና የማዳበሪያ አቅምን በማሳደግ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመቋቋም ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቅ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ሙከራዎች መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፋሲካ ዘለዓለም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሲስተም ኢንጅነሪንግ መጽሐፍ ምረቃ እና የሳታላይት መረጃን ተቀብሎ መተግበር የሚያስችል ኘሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
Next articleአግራ ኢትዮጵያ በግብርናዉ ዘርፍ እገዛ እንደሚያደርግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ የቦርድ ስብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።