
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ሕገ-ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) አንዱ ነው፡፡ ሕገ-ወጥ ንግድ ውስብስብ ሂደት እንዳለው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የቁጥጥር ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ሕገ-ወጥ ንግድ ከሚስተዋልባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ነዳጅ እንደኾነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የነዳጅ ዓመታዊ ፍጆታችን 4 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ብለዋል፡፡ ወደ ውጭ የምትልከው ንግድ በግድ 4 ቢሊዮን ብር የሚሞላው ኢትዮጵያ ነዳጅ ድጎማ ላይ ትኩረት አድርጋ ሠርታለች ብለዋል፡፡
ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቷ የነዳጅ ፍላጎት በየዓመቱ 10 በመቶ እድገት ነበረው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የአሠራር ሥርዓት በማስፈናችን 13 በመቶ ፍላጎቱን መቀነስ ችለናል ነው ያሉት፡፡ ሕገ-ወጥ ንግድ አሁንም ድረስ ግን ሀገራዊ ፈተና በመኾኑ በጋራ እና በትብብር መሥራትን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!