“ስጋቶችን አጥበን፣ እድሎችን አስፍተን፣ እንደ ሀገር ጸንተን መኖር ይገባናል ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

23

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራቶቿን ለመፍታት የዕቅድ ማሻሻያ በማድረግ እየሠራች መኾኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለማሻሻል እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለማስተካከል የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት ላይ ትኩረት አድርጓል ነው ያሉት፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ የተፈጠሩ ስብራቶችን ማሻሻል ሌላው የማሻሻያ ግብ መኾኑንም አንስተዋል።

ምርታማነትን በማስቀጠል የሀገርን እድገት ማምጣት ላይ ግብ አስቀምጦ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ማሻሻያ በችግሮችም ውስጥ ኾኖ ታላላቅ ለውጦች ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን በነበሩት በርካታ ችግሮች የታቀደውን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አልተቻለም ብለዋል፡፡

መንግሥት ካለፈው ሥርዓት የፖለቲካ፣ የእዳ፣ የኢኮኖሚ፣ የሰላም እጦት ስብራት መውረሱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን እኛ አላመጣነውም ብለን ዝም አላልንም እየሠራን ነው ብለዋል። እዳን ለመቀነስ እና ሌሎችን ሥራዎች ለማከናወን እቅዶች ተዘጋጅተው እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ መጪው ትውልድ እዳ ያለባትን ሀገር እንዳይወርስ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የቀረበው በጀት የመጀመሪያውን ዓመት እቅድ ለማሳካት ታሳቢ ያደረገ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የዓለም ፖለቲካ በተስፋና በስጋት የተመላ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስጋቶችን አጥበን፣ እድሎችን አስፍተን፣ እንደ ሀገር ጸንተን መኖር ይገባናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን እድገት ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እይታ አንጻር መመልከት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እድገት የሚታይና የሚዳሰስ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው ንቅናቄ በርካታ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውንና ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡

በርካታ ድሎች እና ስኬቶች ቢመዘገቡም አሁንም የኑሮ ውድነትና ንረት ኢትዮጵያን እየፈተናት መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን ዓለምን እየፈተነ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የእዳ ወለድ ሌላኛው የኢኮኖሚ ችግር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ኾና ሲንከባለል የመጣውን እዳ በታማኝነት እየከፈለች ነውም ብለዋል፡፡

በገቢያ ውስጥ የተረጨውን ገንዘብ መቀነስ ዋጋ ንረትን ለመቀነስ ይረዳናል፤ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ሃብት መቆጣጠር ንረቱን ይቀንሳልም ብለዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን እንደሚፈትንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ አዛኝና ሠራተኛ መኾናችንን ለማረጋገጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝ ይገባልም ብለዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል እና ምርታማነትን ለማስፋት የማዳበሪያ ድጎማ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱን እና የኑሮ ውድነቱን በተቻለ መጠን እየቀነስን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሠራው ሥራ ግን በቂ አይደለም፤ የዋጋ ንረትና እና የኑሮ ውድነትን የሚቋቋም ዜጋ የለንም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በዚህ ክረምት ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ይታረሳል፤ ቢያንስ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከነበረው በተጨማሪ ይታረሳል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ መኾኗንም አስታውቀዋል፡፡ ገቢን ከወጪ እያሳደጉ መሄድ የኑሮ ውድነቱን እና የዋጋ ንረቱን እንደሚቀንሰውም ገልጸዋል፡፡ ገቢን ለማሳደግ እና ወጭን ለመሸፈን ብዙ ሥራዎች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ እየለመኑ ነጻነትን ማጣጣም አስቸጋሪ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የገንዝብ ሥርዓት ለውጥ ማምጣታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሠሩ ሥራዎችም ለውጦች መታየታቸውን ነው የገለጹት፡፡ የብድር አቅርቦት መሻሻሉንም ተናግረዋል፡፡ ሀብትን ወደ ግል ተቋማት መልቀቅ የኢኮኖሚ ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን መንግሥት እንዴት ሊፈታ እንዳሰበ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡
Next article“ሥራ አጥነትን መቀነስ ሰላምን ያመጣል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)