የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ሙስናን መከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

69

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋ ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን በጋራ ለመከላከል የሚያሰችል ስምምነት ተፈራረሙ።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን እና ብልሹ አሠራሮችን በጋራ ለመከላከል የስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት አካሄዱ።

ስምምነቱ የተባበሩት መንግሥታት በብራዚል ባከናወነው ጉባዔ የኦዲትና የፀረ-ሙስና ተቋማት ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን በመከላከል ረገድ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የተደረሰውና ኢትዮጵያ የፈረመችውን ኮንቬንሽን ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል ነው ተብሏል።

የፌዴራል የስነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ተቋማቱ በተናጠል ነፃና ገለልተኛ ሆነው የሚሰሩ ቢሆንም ዛሬ የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ የሕግ አካል ያደረገችውን የዓለም አቀፉን የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ነው።

ሁለቱ ተቋማት መልካም አስተዳደርን ከማስፈ አንፃር ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ከሙስና ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለውን የሀብት ብክነት ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ሥምምነቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ኅላፊ ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት ብልሹ አሰራርን ከመታገልና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር ሚናቸው የጎላ ነው።

ሙስና እንደየሀገራት ባህሪያት ውስብስብ ነው ያሉት ኅላፊዋ የኦዲት ዓላማ የሕዝብ ገንዘብ ለታቀደለት ዓላማ ውለዋል የሚለውን በማጣራት ተጠያቂነትን ማስፈን ነው ብለዋል።

በተናጠል የተሰጡን ኅላፊነቶች ቢኖሩም በጋራ ልናከናውናቸው በማንችልበት ዙሪያ ስምምነት ፈጥረናል ነው ያሉት።

ስምምነቱ የተከናወነባቸው የሥራ መስኮች የተለዩ ሲሆን በየመንግሥት ተቋማት ሙስና ሊከሰትባቸው የሚችልባቸውን በሥራ ዘርፎች ላይ በጋራ ጥናት ማካሄድ፣ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፣ ሙስናን ከመከላከል አንፃር የተሻለ ለሰሩ ተቋማት እውቅና መስጠት፣ በጋራ የባለድርሻ አካላት መድረክ ማዘጋጀት፣ በተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ማድረግና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል። ዘገባው የኢፕድ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚገድቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ እንቅስቃሴዎች ላይ መስራት ድኅነትን ለመቅረፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
Next article“በእርከን ሥራ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በውኃ ማቆር እና በጥንታዊ የእጅ መሣሪያዎች በታወቀው የኮንሶ ሕዝብ መካከል በመገኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ