“የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚገድቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ እንቅስቃሴዎች ላይ መስራት ድኅነትን ለመቅረፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

31

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ጉባዔው በ2016 ረቂቅ በጀት ላይ ነው የተወያየው፡፡

በውይይቱም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ከፍተኛ እድገት እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ የነበረው ጦርነት በሰላማዊ ውይይት መጠናቀቁ እና ሰላምን ለማጽናት ከሚሠሩ ሥራዎች አንጻር የተሻለ እድገት ይኖራታል ተብሎ ይጠብቃል ነው ያሉት፡፡ የተሻለ እድገት እንዲኖር የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ሥራ ይሠራልም ብለዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ምርት ተጨባጭ ለውጥ ታይቷል ነው ያሉት፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ የታዩትን ለውጦች በማስቀጠል እና ችግሮቹን በመፍታት የሀገርን እድገት ማፋጠን እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በችግሮችም ውስጥ ኾና እድገት አሳይታለች ያሉት ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ዓመት ችግሮችን በማቃለል የተሻለ ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሰላም ከቦታ ቦታ ተንቀሰሳቅሶ መሥራት እና ሀገራዊ አንድነትን በማምጣት ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚገድቡ የፖለቲካና የጸጥታ እንቅስቃሴዎችን ማሻሻል ድኅነትን ለመቅረፍ ዋነኛ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድኅነት የሃብት እጦት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ችግሮቹ የሰላም፣ የፀጥታ እና ሌሎች ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ ችግሮችን መፍታት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሁነኛ መሳሪያ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምን በማጽናት መሥራት ከተቻለ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላት ሀገርን መገንባት ይቻላልም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን በማጽናት የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
Next articleየፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ሙስናን መከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።