
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን በማጽናት የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል፡፡
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ሰላም እንዲኖር በመንግሥት በኩል በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የፀጥታ ችግሮች ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን በውይይት እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሕዝቡ የሰላም ባለቤት መኾን አለበትም ብለዋል፡፡ ሰላምን ለማምጣት ከመንግሥት ባለፈ ሕዝቡ እና የፖለቲካ ኀይሎች በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡
ሀገራዊ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት የሁሉም ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡ ሕግ የማስከበር አቅሙም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የቀረበው በጀትም የጸጥታ ተቋማት ሀገራዊ ሰላሙን ለማስከበር ያላቸውን አቅም ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
የውስጥ ሰላምን ማሳደግ ተገቢ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ሀገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ዘላቂ ሰላም ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡ መንግሥትም ኢኮኖሚን ለማሳደግ ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የቴሌኮምንኬሽን አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡ መስሪያ ቤቶች ቁጠባን እንዲለማመዱ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት አቶ አሕመድ ከመስተንግዶ ጋር የሚነሳውን ችግር ቁጥጥር እናደርጋለንም ነው ያሉት፡፡ ክልሎች ኢንቨስትመንት በማሳለጥ ልማትን ማምጣት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!