ከ19 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

54

ሰቆጣ: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማ 75 ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ ዛሬ የክልሉና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።

“የሚስቁ” ተንጠልጣይ የእግረኛ ድልድይ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበትና ከ19 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ድልድይ ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁለተኛው ድልድይ ኾኖ ተመርቋል።

የፅፅቃ ከተማ ነዋሪ ቄስ ሙቀት ታረቀ እንዳሉት ተንጠልጣይ ድልድዩ ከመሠራቱ በፊት ለግብይት ለመንቀሳቀስ እና የመንግሥት ሰራተኞች በስዓቱ ቢሮ ገብቶ ለመውጣት እየተቸገሩ ቆይተዋል። ድልድዩ ከተሠራ በኋላ ግን ይደርስባቸው የነበሩ ጫናዎች መቀነሳቸውንም ለአሚኮ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የፅፅቃ ከተማ ማንጎ ሰፈር ነዋሪ ወይዘሮ ህይዎት ብሩክ የሚኖሩበት ሰፈር ከፅፅቃ ወንዝ ማዶ በመኾኑ ወደ ከተማው ለመሄድ ከ40 ደቂቃ በላይ ዙሮ ወይም በገደል እየወረዱ በመኾኑ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ፣ ገበያና ወደ ህክምና ለመሄድ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ የተሠራው ተንጠልጣይ ድልድይ ኹሉንም ነገር አቅልሎልናል ነው ያሉት።

የዝቋላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ታፈረ ሚሰነ ወረዳው ላይ የመሰረተ ልማት እጥረት በመኖሩ ምክንያት በወረዳው የሚገኙ ሃብቶችን በአግባቡ መጠቀም አለመቻሉን ገልጸዋል። ዛሬ የተመረቀው የሚስኩ የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

አሥተዳዳሪው በቀጣይ የክልሉ መንግሥትም ይሁን ግብረሰናይ ድርጅቶች ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እንዲሠሩላቸው ጠይቀዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የሚሠሩ መሰረተ ልማቶችን ኅብረተሰቡ በአግባቡ መንከባከብና መጠበቅ እንዳለበት ገልጸው የድልድይ ሥራው እንዲሠራ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታደሰ ይርዳው በዘንድሮ ዓመት በዋግኽምራ ሁለት በክልሉ 17 የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮችን ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በክልሉና ሄልቫተስ በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ቢሮ ኀላፊው በቀጣይ ዓመት የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ ተመራጭ እየኾነ እንደመምጣቱ በክልሉ 24 ተንጠልጣይ ድልድዮች ለመሥራት ታቅዷል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሙስናና ብልሹ አሠራር ሀገርን በእጅጉ እየጎዳ በመኾኑ ታግሎ ማስተካከል ከወቅቱ አመራር የሚጠበቅ ነው” የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት
Next articleከህግና አሠራር ውጭ 1 ሺ 519 ግለሰቦች በቤት ማኅበር ተደራጅተው መገኘታቸውን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አስታወቁ።