
ፍኖተ ሰላም፡ ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሕገዎጥ ንግድና የዋጋ ንረትን በመከላከል የኑሮ ውድነቱን ለማስታገስ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
የመምሪያው ተወካይ ኀላፊ አቶ አበበ ድልነሳ በበጀት ዓመቱ 29 ሚሊዮን 480 ሺህ ብር ተዘዋዋሪ ብድር ለሸማች ማኅበራት በማስመደብ የተለያዩ የሰብል እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በ13 ወረዳዎች የሚገኙ የሸማች ማኅበራት የሠሩ ሲኾን ቀሪ የ9 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ሸማች ማኅበራትን በመደገፍ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል እየተሠራ ነው ብለዋል።
እስካሁንም ከ6ሺህ 100 ኩንታል በላይ ጤፍና ለሌሎች የምግብ እህሎች፣ 588 ሺህ 98 ሊትር ዘይት፣ 1 ሺህ 492 ኩንታል ፊኖ ዱቄት፣ 348 ኩንታል ማካሮኒ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶችንና ሸቀጣሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ በሸማች ማኅበራት ቀርበዋል ብለዋል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ እድገት ሸማቾች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ በላይ አክሊሉ፤ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ቡሬ ከሚገኘው ዳሞት ዩኒየን ጋር በተፈጠረላቸው ትስስር ከመሰረታዊ ምርቶች ባሻገር ከ171 ኩንታል በላይ ጤፍ ለመንግሥት ሠራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸውን እና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ማኅበራቸው እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የካፒታል እጥረት ለሸማች ማኅበራት ፈተና መኾኑን የተናገሩት አቶ በላይ መንግሥት አሁንም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የእድገት ሸማቾች ማኅበር ካቀረበው የጤፍ ምርት ሲገዙ ካገኘናቸው የመንግሥት ሠራተኞች መካከል አቶ አዲሱ ወርቁ ተመጣጣኝ በኾነ ዋጋ ምርቱን መግዛታቸው የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋሙ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኛውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል በዋጋ ንረቱ መጎዳቱን የተናገሩት አቶ አዲሱ መንግሥት ሸማች ማኅበራት አስፈላጊውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ድጋፍ ሊያድርግ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የኾኑ ሕገወጥ ንግድና ምርት መደበቅን ለመቆጣጠር በተደረገው ክትትል ከ5ሺህ 290 በላይ የንግድ ድርጆቶች ከቀላል እስከ ከባድ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!