“በቀልን ለባለቤቱ እንተዋለን፣ እኛ ግን የእነርሱን ራዕይ እናስቀጥላለን” የእነ ዶክተር አምባቸው መኮንን ዘመዶች

165

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በሥራ ገበታቸው እያሉ ለተገደሉት ለቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መታሰቢያ ተደርጓል። መታሰቢያ የተደረገው አፅማቸው ባረፈበት በባሕርዳር ደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ነው። መታሰቢያውን ያደረጉት ወዳጅ ዘመዶቻቸው ለሰማዕታቱ መታሰቢያ ደም ለግሠዋል።

መታሰቢያውን ያደረጉት ወዳጅ ዘመዶቻቸው ታሪካቸውን፣ አባትነታቸውን፣ መሪነታቸውን እናስባለን፣ የእነርሱን ታሪክና ራዕይም እናስቀጥላለን፤ ኢትዮጵያ ሰው ያጣችበትን ቀን አለማሰብ ታሪክ አለማስታወስ ነው፤ በቀል የአምላክ ነው፣ እኛ የምንበቀለው ታላቅ ነገርን በማድረግ እና የተሻለ ትውልድ በመፍጠር ነውም ብለዋል። ከጀግና አብራክ የወጡ፣ በጀግንነት የኖሩ፣ ለሀገርና ለሕዝብ የተሰዉ መሪዎች እንደኾኑም አንስተዋል። የሀገር አደራ ተሸክመው፣ ለአደራቸው ታምነው ያለፉ መሪዎች መኾናቸውም በመታሰቢያው ላይ ተነስቷል። ያቺ እለት ጨልማ ትቀራለች መስሎን ነበር፣ ያቺ እለት ብታልፍም ወደን ነበር፣ ያቺ እለት የማታልፍም ትመስል ነበር ሲሉም ቀኗን አስታውሰዋታል።

የቀድሞው ርእሰ መሥተዳድር የዶክተር አምባቸው መኮንን ታናሽ እህት አጀቡሽ መኮንን ሰኔ 15 ቀን ለእኛ ጥቁር ቀን ነች ሲሉ ያስታውሷታል። ዶክተር አምባቸው እንደ አባት ኾነው እንዳሳደጓቸውም አስታውሰዋል። ዶክተር አምባቸው ሃይማኖታቸውን ከዓለም ሕይዎት ጋር አጣጥመው የኖሩ፣ ራሳቸውን ጎድተው ለሀገርና ለሕዝብ የኖሩ ታላቅ ሰው ነበሩም ብለዋል። ከአምባቸው ፍቅር፣ መተሳሰብን፣ ሰላምን እና አንድነትን ነው የተማርነው፣ የአምባቸው ሞት አብዝቶ የሠበረን ደግነታቸው ነው ብለዋል። መልካምነታቸው ሲነሳ እና በትውልድ ሲወሳ ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል። ብዙ ማልቀሳቸውን እና ማዘናቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ አጀቡሽ ከዚህ በኋላ ጠንካራ ኾነን የእርሳቸውን ራዕይ እና ሕልም ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት። የአምባቸውን ደግነት እያስታወሰን እንደ እርሳቸው ደግ እያደረግን እንኖራለንም ብለዋል።

የዶክተር አምባቸው የቅርብ ዘመድ አማረ ሽባባው ዶክተር አምባቸው ትግል ከጀመሩበት ዘመን ጀምሮ ሕይዎታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አንድም ቀን ሰለቸኝ ሳይሉ ለሀገራቸው መሥራታቸውን ተናግረዋል። ከፍተኛ የኾነ የሀገር ፍቅር ያላቸው፣ ከራስ በላይ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስቡ፣ በመነጋገር የሚያምኑ፣ ሁሉንም ሰው በእኩል የሚያዩ ታላቅ ሰው እንደነበሩም አስታውሰዋል። አቶ እዘዝ ዋሴና ምግባሩ ከበደም አቅማቸውን ሳይሰስቱ ለሀገራቸው ለውጥ የታተሩ እና የሰጡ እንደነበሩ ነው ያስታወሱት።

መሪዎቹ ታላቅ ሀገር እንድትኖር በጥንካሬ እንደሠሩም ገልጸዋል። ብዙ መሥራት በሚችሉበት ጊዜ ማለፋቸውንም ገልጸዋል። የመሪዎች ሳይታሰብ ማለፍ ለኢትዮጵያ በተለይም ለአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ጉድለት እንደነበርም ተናግረዋል።
ያልሰከነ ፖለቲካ እና መነጋገርን አለማስቀደም ጀግና መሪዎችን እንዳሳጣም ገልጸዋል። ያልሰከነው ፖለቲካ ሀገሪቱ ሰው እንድታጣ አድርጓልም ነው ያሉት። በመሪዎች ግድያ የአማራ ሕዝብ የመከራ ጊዜዎችን እንዲያሳልፍ እንዳደረገውም ተናግረዋል። የአማራ ችግር ቀጣይ የኾነው ማጣት የሌለብንን ሰዎች በማጣታችን ነውም ብለዋል። ያልተረጋጋ ፖለቲካና ችግር ባለባት ሀገር ጀግና እና ብልህ መሪዎችን ማጣት ለከፋ ችግር እንደሚዳረግም ገልጸዋል። ችግሮች ወደፊትም ይኖራሉ፣ ነገር ግን ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ከመነቃቀፍ ይልቅ መደጋገፍ እና አንድነት ለሀገር እንደሚበጅም ተናግረዋል። መገዳደል ለኢትዮጵያ አይመጥንም፣ ታላቅ ነን ካልን ታላቅ ነገር ማድረግ አለብንም ነው ያሉት። ያለፈው ችግር እንደጎዳን ካወቅን ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ጀግንነታቸውን፣ ታታሪነታቸውን፣ መልካምነታቸውን እናስታውሳለን፣ እየኮራንባቸው እንኖራለንም ብለዋል። ደም የለገሱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውም እነርሱ ደምና ሕይዎት ለሀገር ለግሰዋል፣ እኛ ደግሞ የሰው ሕይዎትን የሚያተርፈውን ደም እንለግሳለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደኾነ የዶክተር አምባቸው መኮነን ፋውንዴሽን ገለጸ፡፡
Next article“በአረንጓዴ አሻራችን ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣው በተተከሉ ችግኞች የሕዝብ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)