
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ረሚ ማርሸዋ እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በኢትዮጵያ ስቴፈን ሎክ (ዶ.ር) ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸው በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎችን የግብርና ሥራ በትብብር ስለመደገፍ እና የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን በዘላቂነት ስለመጠገን አንስተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አማራ ክልል ከፈረንሳይ እና ከመላው የአውሮፓ ሀገራት ጋር የቆየ እና መልካም ግንኙነት አለው ብለዋል። በተለይም ፈረንሳይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አደጋ ውስጥ በወደቀ ጊዜ ድጋፍ ያደረገች አጋር ሀገር ናት ብለዋል። ቅርሱ አሁንም ቢኾን ከአደጋ ያልወጣ እና በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፈ ጥገና የሚያስፈልገው በመኾኑ ያልተቋረጠ እገዛ እንደሚያስፈልግም ዶክተር ይልቃል አንስተዋል። ክልሉ በጦርነት የፈረሱ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና ነዋሪዎችንም በዘላቂነት ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ፈጣን ሥራ ለማከናወን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የአውሮፓ ኅብረት እና የፈረንሳይ መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ረሚ ማርሽዋ በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 18 ሺህ ኩንታል የምርጥ ዘር ድጋፍ እንደሚቀርብ ተናግረዋል። በክልሉ በነበራቸው ቆይታ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ከአርሶ አደሮች ጋር ቆይታ እንዳደረጉም ገልጸዋል። የአርሶ አደሮችን ምርት ለማሳደግ የሚያግዝ ውጤታማ ምርጥ ዘር ለማቅረብ እንደተግባቡም ተናግረዋል። አምባሳደሩ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ተጨማሪ እና ዘላቂ ጥገና እንዲያገኝ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ሳይንሳዊ ጥናት ተሠርቶ ለዩኒስኮ እንደሚቀርብ ተናግረዋል። ቅርሱ ከአደጋ ወጥቶ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጥገና እንዲያገኝ ቀጣይነት ያለው ትብብር እናደርጋለንም ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በኢትዮጵያ ዶክተር ስቴፈን ሎክ የአማራ ክልል የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ኅብረቱ እንደሚደግፍ ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እና በሙሉ ልብ ወደ ልማት ለመግባት የሚደረገውን ጥረት አድንቀው የአውሮፓ ኅብረት በልማት ድርጅቶቹ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!