
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር አበልጽጎ ወደ ሥራ ያስገባው ኢጅፒ የተባለው የግዥ፣ የጨረታ፣ የግብይትና ክፍያ መፈጸሚያ ሶፍትዌር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ያስችላል ተብሏል። ወጪን ለመቆጠብም ምቹ መንገድ እንደኾነ የመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል መተግበሪያው አሁን ላይ በ9 ተቋማት ሥራ መጀመሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ሀጂ ኢብሳ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው ብለዋል። የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሂደቱ በክልል ደረጃ ይጀመራል ያሉት አቶ ሀጂ ኢብሳ የሲዳማ ክልል በስልጠና ላይ ነው ብለዋል። ሁሉም ክልሎች በክልል ደረጃ ካስጀመሩ በኋላ በሂደት እስከ ቀበሌ እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።
አተገባበሩም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ወጭን ለመቆጠብ ምቹ መንገድ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። ይህን መሰል ተግባር ሌሎች ሀገራት ከ5 በመቶ እስከ 25 በመቶ ወጭን ይቀንሱበታል ያሉት አቶ ሀጂ ኢብሳ በተለይ ጨራታ ላይ ላሉ ተግባራት በዲጂታል መልኩ መፈጸሙ አዋጭ ነው ብለዋል።
አተገባበሩ ሌብነትን በመቀነስ፣ ተግባርና ግንኙነትን ወረቀት አልባ ከማድረግ አኳያ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ግዥና ንብረት አሥተዳደር ከአስመጭና ላኪዎች፣ ከሙያ ማኅበራት አባላት፣ ከንግዱ ዘርፍ አካላት፣ ከተቋማት መሪዎችና ሙያተኞች ጋር ውይይት እያደረገም ይገኛል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!