“የማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የማኅበረሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ አድጓል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

67

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና መድኅን ዜጎች በጋራ ባቋቋሙት የጤና ፈንድ ያልታሰቡ የሕክምና ወጭዎችን ለማስቀረት የሚረዳ ስልት ነው።

በአማራ ክልል ማኅበረሰቡ በሕመም ምክንያት የሚያወጣውን ከፍተኛ የሕክምና ወጭ ለመቅረፍ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሃብት አሰባሰብ፣ አሥተዳደርና አጋርነት ዳይሬክተር አዲሱ አበባው ነግረውናል።

በወቅቱ በሦስት ወረዳዎች የተጀመረው አገልግሎት በ2015 ዓ.ም በክልሉ በሚገኙ 184 ወረዳዎች ተደራሽ ተደርጓል። 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚም ኾኗል፡፡ ይህም ፕላን ኮሚሽን ካወጣው የክልሉ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ (የመንግሥት ሰራተኛውን ሳይጨምር) 96 በመቶ ይሸፍናል፡፡

በ2015 ዓ.ም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብም ተችሏል፡፡ ገቢው ከባለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ በ1 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከተሰበሰበው 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፦

➨1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከአባላት
➨300 ሚሊዮን ብር በክልሉ አጠቃላይ ካለው ሕዝብ 10 በመቶ ለሚኾኑት መክፈል ለማይችሉ ዜጎች በክልሉ መንግሥት የተሸፈነ
➨500 ሚሊዮን ብር ደግሞ የክልሉን አፈጻጸም መሰረት አድርጎ በፌዴራል መንግሥት የተሰጠ ድጎማ ነው፡፡

የአባላት ቁጥር በ2014 ዓ.ም ከነበረው 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን በ2015 ዓ.ም ወደ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉና አባላቱ በፊት ከሚያዋጡት ዓመታዊ መዋጮ አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት ታሳቢ ያደረገ ክፍያ በራሳቸው ተነሳሽነት ጭማሪ በማድረጋቸው ከአባላት ለተሰበሰበው ገቢ ማደግ በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያስቀምጠው አንድ ሰው በዓመት ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ 2 ነጥብ 5 ጊዜ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአማራ ክልል ማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ማኅበረሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔው ዜሮ ነጥብ 4 ነበር፤ ለዚህ ደግሞ የጤና ተቋማት ሥርጭት በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የባለሙያና የግብዓት አለመሟላት፣ የመታከሚያ ገንዘብ ችግር በምክንያትነት ተነስቷል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የመታከሚያ ገንዘብ ችግር ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይሁን እንጅ የጤና መድኅን አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ 1 ነጥብ 7 መድረሱን አንስተዋል፡፡ እ.አ.አ በ2030 ሁሉን አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተደራሽነት የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ 2 ነጥብ 5 ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአንድ እጅ ነጻነት፣ በሌላው እጅ ልማት – ወልቃይት”
Next article“በበቂ መጠን እና ዓይነት ምርጥ ዘር ቀርቧል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ